ኢትዮጵያ መድኖች ድሬዳዋ ከተማን 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ በመጀመሪያው ዙር ከተከታያቸው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት በማስፋት አጠናቀዋል።
ድሬዳዋ ከተማ በ18ኛው ሳምንት ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት ቋሚ ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሙኸዲን ሙሳን በሱራፌል ጌታቸው ተመስገን ደረሰን በጀሚል ያዕቆብ ተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ መድን በበኩላቸው በ18ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 1ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል።
የሊጉ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ገና በለጋ ጨዋታ እድሜ ቀዳሚ ለመሆን ሁለቱም ቡድኖች ወደ ፊት የሮጡበትን የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች አስመልክቶናል። በአጋማሹ ብርቱካናማዎቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በወገኔ ገዛኸኝ እና በሀቢብ ከማል ከተደረጉባቸው ሙከራዎች በኋላ በተሻጋሪ ኳስ ያለቀ ኳስ አግኝተው ለግብ የቀረበ አስቆጪ ሙከራ አድርገዋል፤ ከመስመር ተሻገረውን ኳስ መስዑድ መሐመድ ያለቀ አጋጣሚ አግኝቶ ከፍ አድርጎ ካመከነ በኋላ ሌላ አጋጣሚ ለመፍጠር እጅግ ተቸግረዋል። ኢትዮጵያ መድኖችን በአንፃሩ ቀዳሚ ለመሆን በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል እየደረሱ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቢቀጥሉም ጥረታቸውን ወደ ጎልነት ለመቀየር ተጨማሪ ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ሆኖባቸዋል።
ጨዋታው 27ኛ ደቂቃ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። ወገኔ ገዛኸኝ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ሾልኮ በመውጣት በተረጋጋ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎት መድንን መሪ አድርጓል።
ከ9 ደቂቃዎች በኋላም የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት ሲሄዱ መድኖች ኳሱን በረጅሙ አውጥተው በረጅሙ የተጣለውን ኳስ መሐመድ አበራ ፍጥነቱን እና ጉልበቱን ተጠቅሞ በራሱ ጥረት የብርቱካናማዎቹን ተከላካዮች ቀንሶ በግሩም ሁኔታ መሬት ለመሬት በመምታት ክህሎቱን ያሳየ እጅግ ድንቅ ጎል መረብ ላይ አሳርፎ ለመድኖች ገና በመጀመሪያው አጋማሽ እፎይታ የሰጣቸውን ግብ መረብ ላይ አሳርፎ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
በአጋማሹ ኢትዮጵያ መድኖች ፍጹም የጨዋታ እንቅስቃሴ እና የግብ በላይነት መውሰድ ችለው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ብርቱካናማዎቹ ወደ ጨዋታ ሊመልሳቸው የሚችል ጎል ለማስቆጠር ወደፊት በሚሄዱበት እንቅስቃሴ ላይ የመድኖች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ በሚደረጉ አጫጭር እና ረጃጅም ኳሶች ታጅበው ጨዋታው ይበልጥ ግለቱን ጨምሮ ሁለቱም ቡድኖች የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ቢቀጥሉም ጠንከር ያለ አስቆጪ የሚባል አስቆጪ አጋጣሚ ሳያስመለክት የሁለተኛው አጋማሽ አካፋይ አከባቢ ላይ ደርሷል።
ደቂቃው ይበልጥ እየገፋ በሄደ ቁጥር ብርቱካናማዎቹ ጠንከር ብለው በጫና ቢያንስ ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ጎል ለማስቆጠር ቢጣጣሩም ኢትዮጵያ መድኖች ውጤት ወደ ማስጠበቅ ገብተው በእርጋታ ኳስ ተቆጣጥረው በእራሳቸው ሜዳ ላይ መጫወታቸው ቀጥለውም አልፈው አልፈው ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መድረሳቸውን ባለማቋረጣቸው የብርቱካናማዎቹ ጥንካሬ ፍሬ ማፍራቱ ቀርቶ ወደ ተስፋ መቁረጥ አድልቷል።
መድኖቹ በአንፃሩ እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ አደጋዎቹን መፍጠራቸውን የቀጠሉ ሲሆን ከእነዛም መካከል ከማዕዘን ምት የተሻማው ኳስ ተጫራርፎ ከሳጥን ውጪ ወደነበረው ሀይደር ሸረፋ ጋር ደርሶ ከፍ አድርጎ ወደ ግብ የመታውን ኳስ አብዩ ካሣዬ እንዴትም ብሎ ያዳናቸው አጋጣሚ እንዲሁም 84ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ አበራ በግራ መስመር በኩል ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን ገብቶ መሬት ለመሬት መትቶ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ብረት በኩል ያለፈበት ሌላኛው አደገኛ ሙከራ ይጠቀሳል።
ጨዋታው በሁለት ጎሎች ብቻ የሚያበቃ እየመሰለ ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃ ሲያመራ ብርቱካናማዎቹ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን ኢትዮጵያ መድኖች ተጨማሪ ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው ሦስተኛውን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል ፤ 90ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ሚሊዮን ሰለሞን በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አሳርፎ ጨዋታው 3-0 በሆነ ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጓል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ መድን ነጥቡን 35 በማድረስ ከተከታዩ ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 5 በማስፋት የመጀመሪያው ዙር ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ የአሰልጣኝ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ”ሙሉውን ደቂቃው ጥሩ አልነበርንም። ምክንያት መደርደር አልፈልግም ግን እንቅስቃሴያችን ጥሩ ስላልሆነ ራሳችንን ዞር ብለን ዐይተን ባሉብን ክፍተቶች ላይ ሠርተን በእረፍት ቀናት ተጠናክረን እንመለሳለን” የሚል አስተያየት ሲሰጡ የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ”በሞከርነው ልክ ጎል አላስቆጠርንም ከዚህም በላይ ማስቆጠር ነበረብን፤ በአሁኑ አንደኛ ሆነን መጨረሳችን ለቀጣዩ ዋስትና አይሆንም ከዚህም በላይ ሆነን ከዜሮ እንጀምራለን” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።