ሁለቱ የሀገራችን ኢንስትራክተሮች በላይቤሪያ ስልጠና እየሰጡ ነው

በሁለቱ ፆታዎች የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር የሆኑት አብርሃም መብራቱ እና ሰላም ዘርዓይ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የአሠልጣኞች ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።

ሀገራችን ካፈራቻቸው የአህጉሩ ኢንስትራክተሮች መካከል የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና የላይቤሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ሰላም ዘራይ የሚጠቀሱ ሲሆን ሁለቱ ባለሙያዎችም በተለያዩ ወቅቶች በሀገራችን እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ይታወቃሉ። ባለሙያዎቹ አሁን ደግሞ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የካፍ ኤ ላይሰንስ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

በላይቤሪያ ርዕሰ መዲና ሞኖሮቪያ ከተማ እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና ላይ 13 ላይቤሪያዊያን፣ 3 ጋምቢያዊያን እና 1 ዛምቢያዊ ሰልጣኞች እየተሳተፉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም የሁለተኛው ሞጁል የኤ ላይሰንስ ስልጠና በሀገራችን ባለሙያዎች አማካኝነት እየተከታተሉ ይገኛሉ።

የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠናዎች ለተከታታይ አምስት ቀናት የተሰጡ ሲሆን 6ኛ እና 7ኛ ቀናት ላይ ደግሞ ፈተናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ ታውቋል። በስልጠናው ወቅት የመስክ ላይ ትምህርቶች ሲሰጡ ሰልጣኞች የላይቤሪያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን በአካል ተገኝተው የጨዋታ ግምገማ ሪፖርቶችን እንዲሰሩ የተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።

ስልጠናውን የሚሰጡት ሁለቱ ባለሙያዎች በጋራ ከላይቤሪያ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መረጃ ከቀድሞ የላይቤሪያ ተወዳጅ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ጋር እንደተገናኙ ጠቁመው ዊሃ በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ እንዳግባቡና ቃል እንደተገባቡም ገልፀውልናል።

ይሄው የአሰልጣኞች ስልጠና ሦስተኛው ሞጁል ሚያዚያ ላይ አራተኛው እና የመጨረሻው ደግሞ ሀምሌ ወር ላይ ተሰጥቶ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።