ክለብ ዳሰሳ – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የሃምራዊዎቹ ጉዞ መጨረሻ የት ይሆን?

1990ዎቹ አጋማሽ 1 ዙር ጀግና ተብሎ ይጠራ የነበረው ንግድ ባንክ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ጉዞው የቀደመውን መጠርያውን እንድናስታውስ ያስገድደናል፡፡ 80ዎቹ መጨረሻ አንስቶ እስከ 90ዎቹ አጋማሽ እስከ ውድድር ዘመኑ ወሳኝ ወቅት ድረስ የተዋጣለት ቡድን ይዞ የሚቀርበው ንግድ ባንክ ውድድሮች ወደ ወሳኝ ምእራፍ ሲሸጋገሩ ቁልቁል ጉዞ የሚጀምርበት ዘመንን ያስታወሰን የዘንድሮው የክለቡ አቋም እስከ ሻምፒዮንነት ይቀጥላል ወይስ ….. ሶከር ኢትዮጵያ በአጭሩ የውድድር ዘመኑን ተስፋ እና እንቅፋቶች ለመዳሰስ ትሞክራለች

 

2003 የኢትዮጵያ ንግድ ባንከ ለብቻው ጠቅልሎ ከያዘው ወዲህ ክለቡ ከተኛበት መንቃት ጀምሯል፡፡ ድንቅ ተጫዋቾችን በየአመቱ ከማስፈረሙም በላይ ንጉሴ ደስታ እና ውበቱ አባተን በተከታታይ ቀጥሯል፡፡ ከመከላከያ ጋር ጥሩ ጊዜ ያሳለፉት አሰልጣኝ ንጉሴ እና ከቡና ጋር የሊግ ሻምፒዮን የሆኑትን ውበቱ አባተ ቅጥር ክለቡ ለውጤታማነት ያሳየውን ልዩ ተነሳሽነት ያመላክታል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አሰልጣኞች በክለቡ ስኬት ማጣጣም ተስኗቸው በጊዜ የመባረር እጣ ደርሶባቸዋል፡፡

ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተው የተለያዩትን አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ያስፈረሙበት ውሳኔ እጅግ ጠቃሚ እና ውጤታማ እርምጃ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት አመታት ከደረጃው እጅግ እንደመውረዱ እና ለአሰልጣኞች ጊዜ የማይሰጥ ክለብ ከመሆኑ አንፃር የውድድር ዘመኑ ለፀጋዬ ከባድ እንደሚሆን ተገምቶ ነበር፡፡በተለይም ቡድኑ በውድድር ዘመኑ መክፈቻ በአዲስ መጪው ወላይታ ዲቻ የደረሰበት ከባድ ሽንፈት የቀድሞው የሃረር ቢራ እና የትራንስ አሰልጣኝ የባንክ ህይወት አጭር እንዳይሆን ያሰጋ ነበር፡፡

አሁን 9 ሳምንት ላይ ሆነን ስንመለከተው ንግድ ባንክ በሚገባ ያገገመ ይመስላል፡፡ እስከመጨረሻው ደቂቃ የሚዘልቅ የታጋይነት መንፈስ ጥብቅ መከላከል እና ያገኙትን የግብ እድል በአግባቡ መጠቀም የንግድ ባንክ መለያ ሆኗል፡፡

ተስፋዎች

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም

የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያምን ፕሮፋይል ስንመለከት የቀድሞው ድንቅ አጥቂን 10 የውድድር ዘመናት የፕሪሚየር ሊግ ጉዞ በመካከለኛ ክለቦች የተወሰነ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በትራንስ ኢትዮጵያ እና ሀረር ቢራ ድንቅ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን ሲገነቡ በኢትዮፕያ ቡና ለጥቂት ጊዜያት ቆይተዋል፡፡ ኳስ የሚቆጣጠር እና መሃል ለመሃል የሚያጠቃ ቡድን መስራት የሚወዱት ፀጋዬ የንግድ ባንክ ውጤታማነት ቁልፍ ሰው ናቸው፡፡ ከበርካታ አዳዲስ ግዢዎች ጋር ዘንድሮ ቡድኑን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ንግድ ባንክን እያሻሻሉት እንደሆነ በግልፅ ይታያል፡፡ በስብስባቸው የሚገኙትን ተጫዋቾች እንደየጨዋታው ክብደት እና አስፈላጊነት መጠቀማቸው ጠንካራ የተከላካይ መስመር መገንባታቸውና በተጫዋቾች ላይ እምነት ማሳደራቸው ለስኬታቸው አስተዋፅኦ አበርክቶላቸዋል፡፡ የተለያዩ ሲስተሞችን ለመተግበር ያላቸው ድፍረትም መልካም የውድድር ዘመን እንዲያሳልፉ ረድቷቸዋል፡፡

ጥልቀት

የስብስብ ጥልቀቱ ቡድኑ በቀሪው የውድድር ዘመንም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳዋል፡፡ ቡድኑ በሁሉም ቦታዎች በቂ ተሰላፊዎችን ከመያዙ ባሻገር ጥራታቸውም ከአብዛኛዎቹ የተሸለ ነው፡፡ ክለቡ በገንዘብ አቅሙ ጠንካራ በመሆኑ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ግዢዎችን ከፈፀመ በትክክልም በሻምፒዮንነት ፉክክሩ ውስጥ መቆየት ይችላል፡፡

ተጫዋቾቹ አልተዳከሙም

ክለቡ ምንም ተጫዋች ለብሄራዊ ቡድን አለማስመረጡ በትኩስ ጉልበት ለመቅረብ ያስችለዋል፡፡ በሲቲ ካፕ ውድድር እንኳን ሙሉውን ቡድናቸውን ያልተጠቀሙት አሰልጣኝ ፀጋዬ በብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ሳቢያ ከተዳከሙት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ ሲዝኑን በተጠራቀመ አቅም የመጨረስ እድል አላቸው፡፡

ስጋቶች

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለዋንጫ ማጨት እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ ቡድኑ በትልቅ ደረጃ የመፎካከር ልምድ የሌለው ከመሆኑ ባሻገር አሰልጣኙ እስከ መጨረሻው የሚፎካከር ቡድን ያሳዩን በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው (1997 ከትራንስ ጋር 2 ደረጃን አሳክተዋል) ፡፡ ይህ እውነታ ክለቡ የውድድር ዘመኑ ወደ ወሳኝ ምእራፍ በሚሸጋገርበት ወቅት ያሽቆለቁላል የሚል ስጋትን ያሳድራል፡፡

ኤልያስ ማሞ ቢጎዳስ

የዘንድሮው የንግድ ባንክ ድንቅ በኤልያስ ማሞ ድንቅ አቋም ላይ ክፉኛ ተንጠልጥሏል፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ አማካይ 2 የሊግ ግቦችን በስሙ ሲያስመዘግብ ለሌሎች ግቦች መቆጠርም መነሻ ነው፡፡ ፈጣን አንድ ቦታ የማይቆም ድንቅ የኳስ ክህሎት ያለው በአንድ ኳስ ተከላካይ ማስከፈት የሚችል(ከሌሎች ተጫዋቾች አንፃር) እና ከርቀት አክርሮ የመምታት እሎታን የታደለ አማካይ ነው፡፡ 9 ቁጥሩ ከተጎዳ የውድድር ዘመኑ ለንግድ ባንክ እጅግ ፈታኝ ይሆናል፡፡

የማጥቃት አማራጭ

የአሰልጣኙ የማጥቃት አማራጭ ውስን ነው፡፡ ቡድኑ ከመስመር ይልቅ መሃል ለመሃል መጠቀም ሲያዘወተር ኳስ በሚይዙበት ጊዜም የሜዳውን ስፋት በአግባቡ አይጠቀሙበትም፡፡ተጋጣሚዎች የአሰልጣኙን አጨዋወት ተረድተው የሚገቡ ከሆነ ንግድ ባንክን በቀላሉ መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ጨዋታዎች እንደታየው ኤልያስ ማሞ በተካለካይ አማካዮች ቁጥጥር ስር ሲውል በአማራጭ የማጥቃት ስልት እጦት ሲቸገር ይስተዋላል፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ በአጥቂ መስመሩ ፊሊፕ ዳውዚን የመሰለ ግዙፍ ተጫዋች በመያዛቸው የመስመር አጨዋወታቸውን በማሻሻል የመጀመርያ እቅዳቸው ባይሳካ እንደ ሁለተኛ እቅድ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

ቀሪዎቹ ጨዋታዎች

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ አናት ላይ ከሚገኙ ክለቦች እጅግ ፈታኝ እና ወሳኙን ወቅት ለማሳለፍ ይገደዳል፡፡ ምንም ቀሪ ጨዋታ የሌለው ባንክ ከእረፍት መልስ መከላከያን ይገጥማል፡፡ በኳስ ቁጥጥር እና በተደጋጋሚ ሙከራዎች በሊጉ አቻ የማይገኝለት መከላከያ ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ሜዳ የሚገባው ንግድ ባንክን ይፈትነዋል፡፡ 11ኛው ሳምንት ከሻምፒዮኑ ደደቢት ጋር የሚያደርገው ጨዋታም እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ደደቢት ከጊዜያዊ የውጤት ማጣት የማገገሚያ ጊዜ በማግኘቱ ለንግድ ባንክ ፈታኝ ጨዋታ ነው፡፡ 12 ሳምንት ወደ ሃዋሳ ተጉዞ ሀዋሳ ከነማን የሚገጥምበት መርሃ ግብርም ከንግድ ባንክ የሜዳ ውጪ ድክመት አንፃር አስቸጋሪ ጉዞ ይሆንበታል፡፡ ከሶስቱ ፈታኝ ጨዋታዎች በኃላ አንደኛውን ዙር የሚያጠናቅቀው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚያደርገው የባንክ የውድድር ዘመኑ ወሳኝ ጨዋታ ነው፡፡ ባንክ እነዚህን 4 ጨዋታዎች በድል ከተወጣ በእርግጥም የሃምራዊዎቹ ጉዞ አስደሳች ይሆናል፡፡

ግምትአንደኛውን ዙር 3ኛነት ያጠናቅቃል


ቀሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታዎች

10 ሳምንትየካቲት 2 – ከመከላከያወጪ (አአ)

11 ሳምንትየካቲት 9 – ከደደቢትበሜዳው

12 ሳምንትየካቲት 16 – ከሀዋሳ ከነማውጪ

13 ሳምንትየካቲት 23 – ከቅዱስ ጊዮርጊስበሜዳው


*በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ፅሁፎቹን ለሌላ አላማ እንደ ማጣቀሻ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡