ክለብ ዳሰሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የማይገረሰስ የሚመስለው የፈረሰኞቹ ጥንካሬ

መቆራረጥ መለያው የሆነው የኢትዮጵያ ትልቁ ሊግ ከበርካታ ቀሪ ጨዋታዎች እና 2/3 ከሚሆኑ ቀሪ መርሃ ግብሮች ጋር መድረሻው የማይታወቅ ረጅም ጅረት መስሏል፡፡ በይበልጥ ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ትኩረት የምታደርገው ሶከር ኢትዮጵያ አሰልቺውን የሊግ መርሃ ግብር በመቃኘት ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥቂት ምልከታዎች ለመስጠት ትሞክራለች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዘመኑን በድንቅ ሁኔታ እንደመጀመሩ የሁሉም ክለቦች ትኩረት ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ነው፡፡ ቡድኑ በአንዳንድ ጨዋታዎች ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያሳይ በችግር ውስጥ እንኳን ቢሆን የማሸነፍ አእምሮን ተላብሷል፡፡ በርካታ የሊግ ሻምፒዮኖችንና የብሄራዊ ቡድን ቁልፍ ተጫዋቾችን የያዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን የያዘውን አቋም ይዞ መቀጠሉ አጠራጣሪ አይመስልም፡፡

መልካም ጎን

ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከጨዋታ የራቁት ተስፋዬ አለባቸው እና የፍፁም ገብረ ማርያም ወደ ሜዳ መመለስ እና የዮናታን ብርሃኔ ማገገም ለክለቡ አስደሳች ዜና ነው፡፡ በተለይ የአጥቂው ፍፁም መመለስ በኡመድ ኡኩሪ ግቦች ላይ ጥገኛ እየሆነ ለመጣው ቡድን ተጨማሪ አማራጭ ይፈጥራል፡፡ አምና ድንቅ የነበረው ተስፋዬ አለባቸውም ፈጣን የመስመር አማካዮችን ለሚጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሃል ክፍል መረጋጋት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

የስብስብ ጥልቀቱ እጅግ አስደሳች ነው፡፡ አሰልጣኝ ማርት ኑይ በተሰጥኦ በልምድ እና በሃይል የተሞላውን ስብስብ ለሚፈልጓቸው የጨዋታ እቅዶች ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡ የቡድን ጥልቀቱ በቡድኑ ውስጥ ለመሰለፍ የሚደረገውን ፉክክር ሲያጠናክረው ለአሰልጣኙ አቀያይሮ የማጫወት አማራጭንም ይፈጥርላቸዋል፡፡

በተከላካይ ስፍራ የአንጋፋው ደጉ ደበበ እና አይዛክ ኢሴንዴ ጥምረት በቢያድግልኝ ኤልያስ ድንቅ አቋም እና በሳላዲን በርጊቾ መምጣት ምክንያት መመልከታችን ያጠራጥራል፡፡አሰልጣኙ በርካታ አማራጮች በመያዛቸው 3 ተከላካይ መጫወት ቢፈልጉ ወደ መስመር እየወጡ መጫወት የሚችሉት የመሃል ተከላካዮቻቸው ዋስትና ይሆኗቸዋል፡፡ የመስመር ተከላካዮቻቸው ቢጎዱ እንኳን ቢያድግልኝ ኤልያስ የመሸፈን አቅም አለው፡፡ በአማካይ ክፍሉም ለተለያዩ የጨዋታ ሲስተሞች የሚመቹ ተጫዋቾችን ይዘዋል፡፡ የአሰልጣኙ ምርጫ 4-2-3-1 ቢሆንም የአማካይ ክፍል ያለው የተጫዋቾች ክምችት ሌሎች ሲስተሞች ለመተግበር ያመቻቸዋል፡፡

ደካማ ጎን

አብዛኛዎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በብሄራዊ ቡድን ዝግጅት እና የቻን ጨዋታዎች መልስ በስነልቦናው እና አካል ብቃቱ በኩል ወርደው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ከበርካታ ስኬቶች በኃላ የወሳኝ ተጫዋቾች መሰላቸት እና ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በተገኘው ውጤት ጫና ውስጥ የመግባት ስሜት ካሳዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስቸጋሪ ይሆንበታል፡፡ አዳነ ግርማ ምንያህል ተሸመ ደጉ ደበበ በኃይሉ አሰፋ እና አበባው ቡታቆ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች እና በብሄራዊ ቡድን ጉዞዎች በቂ እረፍት አለማድረጋቸውም ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዳያዳክመው ያሰጋል፡፡

በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች የጉዳት ሪከርድም ቡድኑን ያሳስባል፡፡ አሉላ ግርማ ዊልያም አሳንጆ ፍፁም /ማርያም አዳነ ግርማ ደጉ ደበበ እና ዮናታን ብርሃኔ ለጉዳት ተጋላጭ መሆናቸው ቡድኑን ያሳሳዋል፡፡

6 ግቦች የሊጉን የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ሰንጠረዥ እየመራ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪ ቢጎዳ በአጥቂ ስፍራው ላይ የሚኖረው የቅዱስ ጊዮርጊስ አማራጭ መጥበብ የውድድር ዘመኑን ሊያበላሽባቸው ይችላል፡፡ አዳነ ግርማ በአጥቂነት መሰለፍ ካቆመ አመታት መቆጠር መጀመራቸው እና የፍፁም /ምርያም ተደጋጋሚ ጉዳት ለማርት ኑይ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል፡፡

የአሰልጣኙ አዲስነት የውድድር አመቱ እየተጋመሰ ሲሄድ ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመጀመርያ የውድድር ዘመናቸው የሊጉ ሻምፒዮን ያደረጉት የውጭ ሃገር አሰልጣኝ ሚቾ ብቻ ናቸው፡፡ የሊጉን ባህርይ የማያውቁት ሆላንዳዊው ማርት ኑይ ጅማሬያቸው መልካም ቢሆንም ቡድኑ አንዴ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከገባ የመውጫ ብልሃቱ ሊጠፋቸው ይችላል፡፡

ቀሪዎቹ ጨዋታዎች

ቅዱስ ጊዮርጊስ አንደኛውን ዙር ለማጠናቀቅ በብሄራዊ ቡድን ዝግጀት ምክንያት ያልተጫወታቸው 3 ጨዋታዎችን ጨምሮ 7 ጨዋታዎች ይቀሩታል፡፡ ካለፉት 6 ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ወደ ክልል የወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ወደ ደቡብ ይጓዛል፡፡ የክልል ጨዋታዎች አስቸጋሪነት እንዳለ ሆኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነዚህ ጨዋታዎች ፈተና ይገጥመዋል፡፡ ግብ ለማስቆጠር የሚቸገረውና ግብ በቀላሉ የማይቆጠርበት ወላይታ ዲቻ በገዛ ሜዳው የሚጫወት ከሆነ ከክልል ጉዞዎች ፈታኙ ጨዋታ ይሄኛው ይሆንበታል ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ቡድናቸውን ለመደገፍ ወደ ሀዋሳ ሲጓዙ በደረሰ አደጋ ህይወታቸው ያለፈው 3 የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን የሚያስታውሰን ጨዋታም በሀዋሳ ስታዲየም የካቲት 9 ይካሄዳል፡፡ ወጣ ገባ የሚለው የሀዋሳ አቋም ይህንን ጨዋታ ለመግለፅ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ቢሆንም ከሊጉ ወገብ በላይ ከሚገኙ ክለቦች አንዱ በመሆኑ ጨዋታው አስቸጋሪነቱ አያጠያይቅም፡፡ በአንፃራነት በሜዳው የሚጠነክረው አርባምንጭ ከነማም የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈተና ነው፡፡

አዲስ አበባ ላይ ከሚያደርጋቸው ጨዋታዎች መካከል ከደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ለሁለቱ ክለቦች ቀሪውን የውድድር ዘመን ጉዞ የመወሰን አቅም አለው፡፡ ከፈረሰኞቹ ጋር በእኩል ነጥብ ሊጉን የሚመራው ንግድ ባንክ ምንም ቀሪ ጨዋታ የሌለው በመሆኑ የነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ ከባድ ፍልሚያ ያደርጋል፡፡እየዋዠቀ የሚገኘው የአምናው ሻምፒዮን ደደቢትም ወደ ሻምፒዮንነት ፉክክሩ ለመግባት የግድ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ነገር ግን ከደደቢት የዘንድሮ መቀዝቀዝ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ድንቅ አቋም አንፃር የዘንድሮው የኃይል ሚዛን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የማጋደል እድሉ የሰፋ ነው፡፡

ግምትሳይሸነፍ አንደኛውን ዙር በመሪነት ያጠናቅቃል

የቅዱስ ጊዮርጊስ 1ኛው ዙር ቀሪ ጨዋታዎች

1ኛው ሳምንትከሙገርበሜዳው

2ኛው ሳምንትከወላይታ ዲቻውጪ

9ኛው ሳምንትከደደቢትውጪ (አአ)

10ኛው ሳምንት(የካቲት 2) – ከአርባ ምንጭውጪ

11 ሳምንት (የካቲት 9) – ከሀዋሳ ከነማውጪ

12 ሳምንት (የካቲት 16) – ከሀረር ቢራበሜዳው

13 ሳምንት (የካቲት 23) – ከንግድ ባንክወጪ (አአ)

*በድረገፁ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ፅሁፎቹን ለሌላ አላማ እንደ ማጣቀሻ ሲጠቀሙ ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

{jcomments on}