እስካሁን በተካሄዱት የ9 ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ተሞርኩዞ የቅዱስ ጊዮርጊስን የበላይነት ፣ የክልል ክለቦችን እንቆቅልሽ ፣ የደደቢትን ፈተና ፣ የግብ ድርቅን እና የፀጋዬ/ንግድ ባንክን ጥምረት በማንሳት አብርሃም ገ/ማርያም የፕሪምየር ሊጉ የ9 ሳምንታት ጉዞ ምን እንደሚመስል ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
ደደቢት የአምና ክብሩን የማስጠበቅ ፈተና
በሊጉ እስካሁን 6 ጨዋታ ብቻ ያደረገን ክለብ ካሁኑ ከዋንጫ ፉክክር ማውጣት አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ከውጤት አንፃር ካየነው ደደቢት ዘንድሮ በ6 ጨዋታ ያገኘው ነጥብ አምና ሻምፒዮን በሆነበት አመት ከመጀመርያዎቹ 6 ጨዋታዎች ካገነው ነጥብ ጋር እኩል መሆኑ ከቀዝቃዛ አጀማመሩ በጊዜ ሂደት ይነቃል ብለን መገመት እንችላለን፡፡ነገር ግን ከስብስብ እና ከቡድኑ የጨዋታ እንቅስቃሴ የምንረዳው ደደቢት ዘንድሮ ፈተና ውስጥ መግባቱን ነው፡፡ ቡድኑ ባለፉት አመታት የነበረው የስብስብ ጥራት እና ጥልቀት ዘንድሮ አለመኖሩ ለሰማያዊዎቹ ጦረኞች የውድድር ዘመኑን ያከብድባቸዋል፡፡
የአምናው ሻምፒዮን ሊጉ ከመጀመርያዎቹ 3 ጨዋታዎች 9 ነጥብ በመሰብሰብ በጥሩ ሁኔታ ቢጀምርም በሜዳው አርባ ምንጭ ከነማ እና ሙገር ሲሚንቶን ለማሸነፍ እጅጉን ተፈትኗል፡፡ ግቦቹ እንኳን የተቆጠሩት የጨዋታው 2/3ኛ ሰአት ከተገባደደ በኋላ ነው፡፡ባለፉት 3 ጨዋታዎችም ማግኘት ከነበረበት 9 ነጥብ ማሳካት የቻለው 2 ነጥቦች ብቻ ነው፡፡
ቡድኑ አውራ አጥቂው ጌታነህ ከበደ እና በርካታ የግብ እድል የሚፈጥሩት አማካዮች በሃይሉ አሰፋ ፣ አዲስ ህንፃ እና ምንያህል ተሾመን ማጣቱ ለቡድኑ አስፈሪነት መቀነስ ዋና ምክንት ቢሆኑም ቡድኑ ደካማ ሆኗል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ ዳዊት ፍቃዱ ዘንድሮም ግብ በማስቆጠር ተግባር መቀጠሉ ፣ የአማካይ ክፍል ተጣማሪዎቹ ጋብሬል ሻይቡ፣ ታደለ መንገሻ እና ሳምሶን ጥላሁን በጥሩ አቋም መገኘት እና የተከላካይ መስመሩ ከአምናው አለመለወጡ ለቡድኑ የተከታታይ አመት ሻምፒዮንነት ጭላንጭል የተስፋ ምልክቶች ናቸው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወዲሁ ሻምፒዮን ሆኗል?
የዘንድሮው የፈረሰኞቹ አጀማመር እጅግ አስፈሪና ለቀሪ የሊጉ ክለቦች እንቅልፍ የሚነሳ ሆኗል፡፡ ከ6 ጨዋታዎች ሙሉ 18 ነጥብ እና 13 የግብ ልዩነት ሰብስቦ 9 ጨዋታ ካደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በላይ በደረጃው አናት ላይ ተቀምጧል፡፡ ቡድኑ በዚህ ጥንካሬው የሊጉን ክብር ከማሳካት እንደማይመለስ ብዙዎቹ ያመኑ ይመስላል፡፡
ዘንድሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳ ላይ ከሌሎች ክለቦች ጋር ያለው ሰፊ ልዩነት በጉልህ ታይቷል፡፡ ከስብስብ ጥልቀት ጀምሮ እስከ ጥራት እና ልምድ ድረስ ከሊጉ አቅም በላይ የሆነ ይመስላል፡፡ ለወትሮውም ጠንካራ በሆነው ስብስብ ላይ የተጨመሩት ምንያህል ተሾመ ፣ በሃይሉ አሰፋ ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ ፣ ፍፁም ተፈሪ እና ሳላዲን በርጊቾ ቡድኑን ወደ ፍፁምነት አቅርበውታል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ ለተከታታይ 2 የውድድር ዘመናት የሊጉን ዋንጫ አጥቶ አያውቅም፡፡ አንድ የውድድር ዘመን ካለስኬት ሲጠናቀቅ በክለቡ ውስጥ የሚነግሰው አስደናቂ ተነሳሽነት ለዘንድሮው ሻምፒዮንነት ተጨማሪ ተነሳሽነት ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡
የክለቡ አንፃራዊ መረጋጋት ሌላው ለሻምፒዮንነት ጠቋሚ ከሚሆኑ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ የአምናው ሻምፒዮን ደደቢት ለክብር ያበቁት ወሳኝ ተጫዋቾች መልቀቃቸው ፣ በርካታ አንጋፋዎችን አሰናብቶ በወጣቶች የተዋቀረው ኢትዮጵያ ቡና በሽግግር ላይ መሆኑ እና መከላከያ ፣ ሀዋሳ ከነማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጥነት ማጣት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለማድላት በቂ ምክንያት ይሆናል፡፡
ባንክ ትክክለኛውን ሰው አግኝቷል?
በውድድር ዘመኑ መክፈቻ በአዲስ መጪው ወላይታ ዲቻ 4-0 ሲረመረም ለተመለከተ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮም ላለመውረድ የሚታገል ቡድን ይመስል ነበር፡፡ ከዛ ጨዋታ ወዲህ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ጠንካራው ንግድ ባንክን ቀስ በቀስ እየሰሩት ነው፡፡
ፀጋዬ በትራንስ ኢትዮጵያ እና ሀረር ቢራ የሰሩትን ያህል መልካም እግርኳስ የሚጫወት ቡድን ባይሰሩም በሩብ የውድድር ዘመን በክለቡ የፈጠሩት ለውጥ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ቡድኑ በአንድ ጨዋታ ከ 1ግብ በላይ ማስቆጠር ቢከብደውም በቀላሉ ግብ የማይቆጠርበት የተከላካይ መስመር ገንብተዋል፡፡ ንግድ ባንክ ከእረፍት በፊት ግብ አስቆጥሮ ለበርካታ ደቂቃዎች ግቡን ሳያስደፍር ውጤት አስጠብቆ የመውጣት ብርታትን ያገኘው በፀጋዬ አመራር ነው፡፡
የፀጋዬ ንግድ ባንክ የዘንድሮ ትልቁ ጥንካሬ እንደ ቡድን መጫወቱ ቢሆንም የአንዳንዶቹን ተጫዋቾች የተናጠል ብቃት እንዲያሻሽሉ ረድተዋቸዋል፡፡ አምና ከደደቢት ተዛውሮ የተጠበቀውን ያህል መሆን ያልቻለው ፊሊፕ ዳውዚ ዘንድሮ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡ በተክለ ሰውነቱ ከሌሎች አንሶ የሚታየው ኤልያስ ማሞ ድንቅ የጨዋታ አቀጣጣይነቱ ፣ የመተጣጠፍ ብቃቱ ፣ በማጥቃት ወረዳ የሚያደርገው አንፃራዊ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ እና ከርቀት ወደ ግብ የሚመታቸው ኳሶች ጥንካሬ የቡድኑ የልብ ምት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ከሃረር ቢራ የመጣውና ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር የተገናገው ቢንያም ሲራጅም በተከላካይ ክፍሉ ጉልህ ልዩነት ፈጥሯል፡፡
የክልል ክለቦች ህይወት ከብዷቸዋል
ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀሉት እንግዶቹ ወላይታ ዲቻ እና ዳሸን ቢራን ጨምሮ 7 የክልል ክለቦች የሊጉ ተሳታፊ ናቸው፡፡ክልል ክለቦች ከሜዳዎቻቸው አስቸጋሪነት እና ካላቸው ሰፊ የደጋፊ መሰረት ጋር ተዳምሮ በሊጉ አዲስ አበቤዎችን እንደሚፈትኑ ቢጠበቅም ከግምት በተቃራኒ እየተጓዙ ነው፡፡
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ እስከ 5 ባለው ደረጃ የሚገኘው የክልል ክለብ ሀዋሳ ከነማ ብቻ ሲሆን የክረምቱ ከፍተኛ ገንዘብ አውጪ ዳሸን ቢራ አንድም ግብ ሳያስቆጥር 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ወላይታ ዲቻ እስካሁን ሽንፈት ባያስተናግድምግብ ማስቆጠር የቻለው በ2 ጨዋታዎች ብቻ ነው ፤ ዳሸን ቢራ ሊጉን ለመልመድ ተቸግሯል ፣ ሀረር ቢራ በማያልቅ ውዝግብ ውስጥ ተዘፍቋል ፤ አርባምንጭ ከነማ እና ሙገር ሲሚንቶ ከአንድ ጨዋታ ወደ ሌላው በተሸጋገሩ ቁጥር ወጥ አቋም ማሳየት ተስኗቸዋል ፤ የሲዳማ ቡና እንቅስቃሴም ለከርሞ ወደ ብሄራዊ ሊግ እንዳያመራ ያሰጋል፡፡ በአንፃራዊነት ሀዋሳ ከነማ በተከታታይ አሸንፎ ወደ መሪዎቹ የመጠጋት ምልክት ቢያሳይም ያለፉትን 2 ጨዋታዎች አቻ መውጣቱ ግስጋሴውን አደብዝዞታል፡፡
ለወትሮውም የክልል ክለቦች ለሻምፒዮንነት የሚፎካከሩት ከአመታት አንዴ ነው፡፡ በ16 አመታት የሊጉ ጉዞ የአአ ክለቦችን ለዋንጫ ሲገዳደሩ ወይም ሻምፒዮን ሲሆኑ የተመለከትነው በጥቂት አጋጣሚዎች ነው፡፡ በ1995 አርባ ምንጭ(2ኛ) ፣ በ1996 ሀዋሳ ከነማ(1ኛ) ፤ በ1997 ትራንስ ኢትዮጵያ(2ኛ) ፣ በ1999 ሀዋሳ ከነማ(1ኛ) እና በ2003 ሲዳማ ቡና(4ኛ) ላይ ከተመለከትናቸው የሻምፒዮንነት ፉክክሮች ውጪ የክልል ክለቦችን ጥንካሬ ለማየት አልታደልንም፡፡
የጎል ድርቅ አሳሳቢ ሆኗል
በሊጉ ዘንድሮ 55 ጨዋታዎች ተደርገው 83 ግቦች ተቆጥረዋል፡፡ በጨዋታ 1.5 ግበ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ጨዋታው 1-0 አልያም 0-0 የመጠናቀቅ ሰፊ እድል አለው፡፡ ከጨዋታዎች 1/3ኛ የሚሆኑት 0-0 ሲጠናቀቁ 56% ጨዋታዎች ላይ ከ 1 በላይ ግብ ለማየት አልታደልንም፡፡
ለጎል ድርቁ በርካቶች የሜዳዎችን አስቸጋሪነት እንደ ምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡ ‹‹ ትልቁን ›› አአ ስታዲየም ጨምሮ የሜዳዎቹ ጎርባጣነት በክፍት ጨዋታ ግብ ለማስቆጠር አዳጋች አድርጎባቸዋል፡፡ የአንዳንድ ክለብ አሰልጣኞች በቅርቡ ሲያማርሩት የሰነበቱት የመጫወቻ ኳሶችም እክል እንደፈጠረባቸው ያምናሉ፡፡
ምክንያቶቹን እንደ ምክንያት ብንቀበልም ብቸኛ ምክንያት አድርጎ መቀበል እጅግ ያስቸግራል፡፡ የቡድኖቻችን የቆመ ኳስ አጠቃቀም ደካማነት ፣ ደካማ የታክቲክ አቀራረብ እና የአሰልጣኞች ግልፅ የጨዋታ እቅድ አለመኖር ከሜዳዎቹ አስቸጋሪነት በላይ በጉልህ የሚታይ ችግር ነው፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ