የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሙሉ ማክሰኞ እለት ተካሂደዋል፡፡ በመሸናነፍ በተጠናቀቁት ሁሉም ጨዋታዎች 20 ግቦች ከመረብ አርፈዋል፡፡
በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ 9፡00 ላይ መብራት ኃይልን የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና በቀላሉ 3-0 አሸንፏል፡፡ ለአደገኞቹ የድል ግቦቹን የመስመር አጥቂው አስቻለው ግርማ ፣ የዘንድሮው የቡና ከፍተኛ ግብ አግቢ ኤፍሬም አሻሞ እና አስቻለው ግርማን ቀይሮ የገባው ኤፍሬም ዘካርያስ ከመረብ አሳርፏል፡፡
በ11፡30 የቡና እና መብራትን ጨዋታ ተከትሎ በተካሄደው ጨዋታ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ግርጌ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድንን 2-1 አሸንፏል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ፈረሰኞቹ ሲሆኑ ግብ አስቆጣሪው ኡመድ ኡኩሪ ነበር፡፡ መድን ለእረፍት ከመውጣታቸው በፊት በወሰኑ አሊ ግብ አቻ መሆን ቢችልም በ78ኛው ደቂቃ ደጉ ደበበ ከቅጣት ምት ያስቆጠራት ድንቅ ግብ ፈረሰኞቹን ለድል አብቅታለች፡፡
በክልል በተካሄዱ ጨዋታዎች ወደ ሐረር ያቀናው ሀዋሳ ከነማ ሐረር ሲቲን በታፈሰ ተስፋዬ እና አንዱአለም ንጉሴ ግቦች 2-0 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ይርጋለም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 3ኝነት ከፍ አድርጓል፡፡ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ፣ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ደደቢትን ፣ ፋሲለደስ ላይ መከላከያ ዳሽን ቢራን በተመሳሰይ 2-1 የረቱበት ጨዋታዎች ሌሎች የ18ኛው ሳምንት ውጤቶች ናቸው፡፡
ሊጉን አንድ ጨዋታ ብቻ የተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ51 ነጥቦች ሲመራ ኢትዮጵያ መድን በ9 ነጥቦች የመጨረሻውን ደረጃ ይዛል፡፡
{jcomments on}