የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25 ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ የክልል ጨዋታዎችም በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተጠናቀዋል፡፡
ሐረር ላይ ከፕሪሚየር ሊግ መውረዱን ያረጋገጠው ሐረር ሲቲን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ተሸንፏል፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይህ ሽንፈት በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ሽንፈት ሆኖ ሲመዘገብ ለሐረር ቢራ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያስመዘገበው የመጀመርያ ድል ሆኗል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም መብራት ኃይልን 1-0 ያሸነፈው መከላከያም እንደ ሐረር ሲቲ ሁሉ መብራት ኃይል ላይ ያስመዘገበው የመጀመርያ የሊግ ድል ሆኗል፡፡
ቦዲቲ ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 2-1 በማሸነፍ የአንደኛውን ዙር ሽንፈት ተበቅሏል፡፡ ድቻ በሊጉ የመጀመርያ ሽንፈቱን ያስተናገደው በደደቢት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ሲዳማ ላይ ሲዳማ ቡና አሁንም በጥንካሬ ዘልቋል፡፡ ዳሽን ቢራን 1-0 አሸንፎም ከንግድ ባንክ ያለውን ርቀት አጥብቦ በ3ኝነት ለማጠናቀቅ ያለውን ተስፋ አለምልሟል፡፡
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ሙገር ሲሚንቶን 2-1 አሸንፏል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠረባቸው ግብ 1-0 ሲመሩ የቆዩት አርባምንጮች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች አሸንፈው ወጥተዋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ መድንን 1-0 አሸንፏል፡፡ ለኢትዮጵያ ቡና ኤፍሬም አሻሞ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡
ትላንት በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከነማን አዲ አበባ ስታድየም ላይ ያስተናገደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለ ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡