ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና የአሰልጣኝ ጥላሁንመንገሻን ቅጥር ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጰያ ቡና በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ እንዲህ ባለ መልኩ ይፋ አድርጓል፡፡
‹‹ አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ አሁን የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የወንዶች ዋናው ቡድንን በሁለት አመት የውል ኮንትራት በ100000/አንድ መቶ ሺህ ብር/ ለማሰልጠን ተስማምቷል ፡፡ በቀጣይ ቀናትም ያሉትን እና ወደ ክለቡ የሚቀላቀሉ ተጫዋቾች በማየት ወደ ስራ ይገባል ፡፡ ››
በተጨማሪም የጳውሎስ ጌታቸው ምክትል የነበሩት መርሻ ሚደቅሳን ተክቶ የቀድሞው የመብራት ኃይል እና የኢትዮጵያ ቡና ድንቅ አማካይ አንዋር ያሲን የጥላሁን መንገሻ ምክትል እንደሚሆን ክለቡ አስታውቋል፡፡ አንዋር በአሁኑ ወቅት በባህርዳር ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ በሚደረገው ውድድር አዲስ አበባ ከነማን ይዞ ተጉዟል፡፡
አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የጠበቀ ቁርኝት አላቸው፡፡ በተጨዋችነት ለረጅም ጊዜ አደገኞቹን ከማገልገላቸውም በላይ በአለሰልጣኝነት 2 ጊዜ ቡድኑን ተረክበው አሰልጥነዋል፡፡ በ1996 የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ስንብት ተከትሎ ክለቡ ለ1 የውድድር ዘመን ያሰለጠኑ ሲሆን በ2000 አም የመውረድ አደጋ ተጋርጦበት የነበረውን ቡድን ተረክበው በ5ኝነት እንዲያጠናቅቅ ረድተውታል፡፡
ፎቶ – በ Ethiopian coffee sport club team page