ንግድ ባንክ ከከፍተኛ ሊጉ ሦስት ተጫዋች ለማስፈረም ተቃርቧል

ንግድ ባንክ ከከፍተኛ ሊጉ ሦስት ተጫዋች ለማስፈረም ተቃርቧል

የዓምና የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከከፍተኛ ሊጉ ሦስት ተጫዋቾን የግሉ ለማድረግ ተቃርቧል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንደኛው ዙር ካደረጋቸው አስራ ሰባት ጨዋታዎች ሃያ ሁለት ነጥቦችን በመሰብሰብ አስራ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ዙሩን ማጠናቀቁ ይታወቃል። ለሁለተኛው ዙር ቡድኑን ለማጠናከር እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ንግድ ባንክ ሦስት ተጫዋች ከከፍተኛ ሊግ ለማስፈረም መስማማቱን አውቀናል።

ክለቡን የተቀላቀለው የመጀመርያ ተጫዋች አጥቂው ናትናኤል ዳንኤል ሲሆን በያዝነው ዓመት በቤንች ማጂ ቡና ጥሩ ቆይታ የነበረው አጥቂው ከዚህ ቀደም በዱራሜ ከተማ ፣ በቡራዩ ከተማ መጫወት ችሏል

ሁለተኛው ለቡድኑ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ የሚጠበቀው አማካዩ ዘላለም አበበ ሲሆን ከዚህ ቀደም በጅማ አባባቡና ዘንድሮ ደግሞ በሀላባ ከተማ ሲጫወት መቆየቱ ይታወሳል።

ሌላው ቡድኑን የተቀላቀለው ሦስተኛ ተጫዋች አማካዩ በዛብህ ካቲሶ ሲሆን በዱራሜ ከተማ ጥሩ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ በመጨረሻም ወደ ሊጉ ክለብ ለመቀላቀል መቃረቡ ታውቋል።

ሦስቱም ተጫዋቾች ያለፉትን ሁለት ሳምንት ከቡድኑ ጋር አብረው ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዮ ሲሆን ከሰሞኑ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።