በሞሮኮ ለሚዘጋጀው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ መርሐግብርን ከ ዩጋንዳ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በድምር ውጤት 2ለ2 በተሰጠው የመለያ ምት ደግሞ 5ለ4 በማሸነፍ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በመጀመሪያው የካምፓላ ጨዋታ ላይ ሉሲዎቹ የተጠቀሙትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ሲቀርቡ በአንጻሩ ዩጋንዳዎች ግብ ጠባቂዋን ሩዝ አቱሮን በዳይሲ ናካዚ በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪያቸው ሆኗል። በናይጄሪያዊቷ የመሐል ዳኛ ፔሸንስ ንዲዲ መሪነት በጀመረው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ብልጫን ቢይዝም ጥንቃቄ ላይ አመዝነው የተንቀሳቀሱትን የዩጋንዳን የኋላ አጥር ሰብሮ መግባቱ ላይ በመጠኑ ሲቸገሩ ተመልክተናል።
ከአማካይ ክፍሉ በሚመነጩ ኳሶች ከመስመር መነሳትን መርጠው የሚጫወቱት ሉሲዎቹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚስዋሉባቸው ተደጋጋሚ ጥድፊያዎች እና ሴናፍ በተደጋጋሚ የምታገኛቸውን ያለቀላቸውን ኳሶች ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ውስጥ በመገኘቷ የተገኙ ዕድሎች ወደ ግብነት እንዳይለወጡ አድርጓል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ማዕድን በጥሩ የእግር ስራ የሰጠቻትን ሎዛ ወደ ግራ ላደላችው አረጋሽ አቀብላ በዩጋንዳ ተከላካይ የተመለሰው ኳስ የግቡን ቋሚ ብረት ገጭቶ ተመልሷል።
በሜዳቸው ያገኟትን ሁለት ግቦች አስጠብቆ መውጣት ላይ በይበልጥ ያተኩሩ እንጂ ኳስ እግራቸው ስር ሲገባ በመልሶ ማጥቃት ተቃራኒ ሜዳ ላይ ፈጥነው የሚደርሱት ዩጋንዳዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ፋዚላ ኢክዋፑት አደገኛ ሙከራን ሰንዝራ በግቡ የቀኝ አግዳሚ በኩል ኳሷ ታካ ወጥታለች። ጨዋታው ቀጥሎ ሎዛ አበራ ሁለት ሙከራዎች ስታደርግ በተለይ 41ኛው ደቂቃ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ከግብ ዘቧ ዳይሲ ናካዚ ጋር ተገናኝታ ሲመለስባት 45ኛው ደቂቃ ደግሞ ዩጋንዳዎች በፒዮና ናቡምባ አማካኝነት ጠጣር ሙከራን ቢያደርጉም የታሪኳ በርገና ንቃት ኳሷን ከጎልነት ታድጋታለች።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ አጀማመሩ መጠነኛ መቀዛቀዞች ቢኖሩርም ቀስ በቀስ ግን የኢትዮጵያ የበላይነት የተንፀባረቀበት ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ባደረገችው እና ግብ ጠባቂዋ ዳይሲ ናካዚ ባመከነችው ኳስ አጋጣሚን የፈጠሩት ሉሲዎቹ 55ኛው ደቂቃ ላይ የዩጋንዳዋ ወሳኝ አጥቂ ፋዚላ ኢኪዋፑት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከወጣች በኋላ የጨዋታ የበላይነት ይኖራቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም መጓጓቶች እና ጥድፊያዎች ቡድኑ ላይ ተፅእኖን ሲፈጥር ተመላክቷል።
66ኛው ደቂቃ ላይ ራሳቸው ያስጀመሩትን ኳስ በዩጋንዳ ተከላካዮች ተመልሳ ወደ ግራ አቅጣጫ የመጣችን ኳስ መሳይ ተመስገን በረጅሙ ስታሻግር አረጋሽ ካልሳ ከሳጥን ጠርዝ የመታቻን ኳስ መረቡ ላይ አርፋ ኢትዮጵያን መሪ አድርጋለች። ከጎሏ መቆጠር በኋላ የጨዋታው ግለት ከፍ እያለ ይመጣል የሚል ግምት ቢኖርም አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ሎዛ አበራ እና አረጋሽ ካልሳን የወሰዱት ፈጣን ቅያሪ የኋላ ኋላ ዋጋ ያስከፈላቸው ይመስላል።
ወደ መጨረሻዎቹ ሃያ ያህል ደቂቃዎች ሲሻገር ደካማ እንቅስቃሴን ሲያስመለክተን የነበረው ጨዋታ ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ 90+7′ ላይ ደርሶ ኢትዮጵያን ያስፈነደቀች ጎል ተገኝታበታለች። ከቀኝ በኩል ወደ መስመር ከተጠጋ ቦታ የተገኘን የቅጣት ምት እጸገነት ግርማ በቀጥታ መትታ ማራኪ ጎል አድርጋው ጨዋታው 2ለ0 በድምር ውጤት ደግሞ 2ለ2 መጠናቀቁን ተከትሎ በመጨረሻም በተሰጠው የመለያ ምት ሉሲዎቹ በግብ ዘቧ ታሪኳ በርገና ብቃት ታግዘው 5ለ4 በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሁለት ዘጠና ደቂቃ ወደ ሚጠብቃቸው ጨዋታ አልፈዋል።