ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ዓ.ዩን ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ በነጥብ መጋራት ተጠናቋል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገው ዋና ዳኛ ፍቅሩ ለገሰ መሪነት የተካሄደው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተሽለው የታዩበት ሲሆን ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግም ቀዳሚ ነበሩ፤ ሀብታሙ ታደሰ ከመስመር ወደ ሳጥኑ አሻግሯት መስፍን ታፈሰ መቷት ግብ ጠባቂው በረከት አማረ የመለሳት ኳስም ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።
በ14ኛው ደቂቃም የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አስቻለው ሙሴ ከቀኝ መስመር አሻምቷት ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ ያስቆጠራት ኳስም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ወልዋሎዎች በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ተሽለው የተንቀሳቀሱበት ነበር። የአብሥራ ሙሉጌታ በሁለት አጋጣሚዎች በግንባር ያደረጋቸው ሙከራዎችም እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በተለይም ከቆመ ኳስ ተሻምታ ተከላካዩ በግንባር ገጭቷት ግብ ጠባቂው እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣት ሙከራ ወልዋሎን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።
እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ ሳቢ እንቅስቃሴ አልተደረገበትም። አጋማሹ በተጀመረ በስምንተኛው ደቂቃ በወልዋሎ ሳጥን ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተገኘው የፍፁም ቅጣት ምት መስፍን ታፈሰ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ደካማ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል ሳሙኤል ሳሊሶ ከግቡ አፋፍ ሆኖ ያመከናት ኳስ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በግንባር ባደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ወልዋሎዎች በበኩላቸው በሳሙኤል ዮሐንስ የረዥም ርቀት ሙከራ ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ዳዋ ሆቴሳ በሲዳማ ቡና ሳጥን ውስጥ በግብ ጠባቂው አማካኝነት ራሱ ላይ የተሠራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኛትን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ብዙም ማራኪ እንቅስቃሴ ባልታየበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በጨዋታው መጀመሪያ እና ማጠናቀቂያ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ግቦች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።