በአሰልጣኝ በረከት ደሙ የሚመሩት አርባምንጭ ከተማዎች የሁለት አጥቂዎችን ዝውውር አጠናቅቀዋል።
በ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ዙር በሃያ አራት ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀው አርባምንጭ ከተማ በነገው ዕለት ፋሲል ከነማን በሁለተኛው ዙር የሃያኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐግብሩን ከማስተናገዱ በፊት የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቅቋል።
ፀጋዬ አበራ ቡድኑን በይፋ መቀላቀል የቻለ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። ከአርባምንጭ ከተማ ከተገኘ በኋላ በወላይታ ድቻ ፣ ሲዳማ ቡና እና ላለፈው አንድ ዓመት ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ቆይታ ያደረገው የመስመር እና የፊት አጥቂው ወደ ቀደመ ክለቡ መመለሱ ተረጋግጧል።
ሌላኛው ቡድኑን የተቀላቀለው ታምራት እያሱ ነው። ከከፍተኛ ሊጉ ነገሌ አርሲ ከተገኘ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ የአንድ ዓመት ቆይታን ያደረገው እና በክለቡ እምብዛም ግልጋሎት ያልሰጠው አጥቂ ወደ ትውልድ ሀገሩ አርባምንጭ ያመራ ሁለተኛው ተጫዋች ሆኗል።