ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምሯል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምሯል

የኮንኮኒ ሀፊዝ ብቸኛ የግንባር ጎል ኢትዮጵያ ቡና ስሑል ሽረን በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ 1ለ0 አሸናፊ እንዲሆን አስችሎታል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አጀማመሩ ተመጣጣኝ ቢመስልም ኢትዮጵያ ቡናዎቹ በሦስቱ ዋነኛ የማጥቂያ ቦታዎች ላይ እያሳዩ የመጡትን የበላይነት ተከትሎ ብልጫው የወሰዱ ቢሆንም በሙከራ ረገድ ግን ቀዳሚዎቹ ስሑል ሽረዎች ናቸው። 5ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ አዳሙ ከተገኘበት የግራ የሳጥኑ ክፍል ያገኘውን ኳስ መቶ በግብ ዘቡ ዳላንድ ኢብራሂም የተመለከተበት አጋጣሚ ተጠቃሿ ሙከራቸው ሆናለች።

ከአማካይ ክፍል ይመነጩ የነበሩ ኳሶችን ወደ መስመር በመለጠጥ በጥልቅ ተስበው ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ቡናማዎቹ 8ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ ዲቫይን ዋቹኩዋ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ኮንኮኒ ሀፊዝ በግንባር በመግጨት መረብ ባሳረፋት ኳስ መሪ መሆን ችለዋል።

የተጋጣሚያቸው ሳጥን አካባቢ አብዛኛውን ጊዜ ማሳለፋቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ ተጨማሪ ጎል ወደ ቋታቸው ለመክተት በድግግሞሽ ሲያጠቁም አስተውለናል። በ23ኛው ደቂቃ ዲቫይን ዋቹኩዋ ከማዕዘን አሻምቶ ወልደአማኑኤል ጌቱ በእግሩ የመለሳትን ኳስ ኮንኮኒ ሁለተኛ ጎል አደረገ ተብሎ ሲጠበቅ አብዱለጢፍ መሐመድ ከመስመር ላይ ያወጣት እጅግ ለግብ የቀረበች የቡድኑ ሙከራ ነበረች።

በብዙ ረገድ ለመበለጥ የተገደዱት እና ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መድረስ ላይ ድክመት የነበረባቸው ሽረዎች 35ኛው  ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት አብዱለጢፍ መሐመድ ሙከራን ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ዳላንድ ኢብራሂም ያዳነበት አጋጣሚ ከረጅም ደቂቃዎች በኋላ ቡድኑ ያደረገው አደገኛ ሙከራ ሆናለች።

ከዕረፍት መልስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ካደረጉት እንቅስቃሴ አኳያ ተመጣጣኝ አቀራረብን መመልከት ብንችልም በአጋማሹ ግን አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አልተመለከትንበትም።

ስሑል ሽረዎች ወደ ጨዋታ እንዲመልሳቸው በሽግግር ከተከላካይ ጀርባ በሚወረወሩ ኳሶች ጎልን ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን የጨዋታ መንገድ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያውን በመስጠት አሁንም በይበልጥ ለሳጥን ቀርበው በመንቀሳቀሱ ሻል ያለ ቅርፅ ቢኖራቸውም የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የተመለከትናት ብቸኛዋ ጎል ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ነጥብን እንዲያገኝ አስችላ ጨዋታው ተጠናቋል።