ሪፖርት | ዓድዋን በማሰብ የተጀመረው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

ሪፖርት | ዓድዋን በማሰብ የተጀመረው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

በጎል ሙከራዎች ያልታጀበው የድሬዳዋ ከተማ እና መቻል ጨዋታ 0ለ0 ተቋጭቷል።

ዓድዋን በሚዘክሩ ሁነቶች የጀመረው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ላቅ ያለ ፉክክር ቢያስተናግድም በሒደት ግን አጋጣሚዎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በንፅፅር የሽግግር አጨዋወት ላይ ትኩረት አድርገው ሦስተኛው ሜዳ ላይ በመገኘት የተሻሉ የነበሩት መቻሎች በ4ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ዮዳሄ አሻምቶ ፍሪምፓንግ በግንባር ገጭቶ በአግዳሚ ብረት በኩል ታካ ኳሷ የወጣችበት  እንዲሁም ደግሞ በአንድ ለአንድ ግንኙነት አብዱልከሪም ከተከላካይ ጀርባ የደረሰውን ኳስ በግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ የመከነበት አጋጣሚ በተጠቀሱት ደቂቃዎች ውስጥ የተደረጉ የጎሉ ሙከራዎች ነበሩ።

ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ሲቸገሩ የሚስተዋሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን በአንድ አጋጣሚ ከማምራታቸው ውጪ የፈጠሩት ልዩነት አልነበረም። መሪ የሚያደርጋቸው ግብ ለማስቆጠር ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በይበልጥ ለሳጥኑ ቀርበው የተንቀሳቀሱት መቻሎች 39ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ካደረጋት ደካማ ዕድል በኋላ አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል።

በሁለተኛ አጋማሽ በተመለሰው ጨዋታ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች በቀር የግብ አጋጣሚዎችን ያላስተዋልንበት ሆኗል። ተመጣጣኝ የፉክክር መንፈስን ነገር ግን ጥራት ያላቸው ዕድሎች ሳይፈጠሩበት መጓዙን የቀጠለው ጨዋታው መቻሎች ወደ መስመር ባደላ ድሬዳዋዎች በአንፃሩ መሐል ለመሐል እና ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች ግብን ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ማየት ብንችልም ወደ መጨረሻው ደቂቃ ከተፈጠሩ ሁለት ሙከራዎች ውጪ ተጨማሪ ነገር ጨዋታው አልነበረውም።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል በ78ኛው ደቂቃ አብዱሰላም ከቅጣት አሻምቶ ሱራፌል በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት እና 84ኛው ደቂቃ ዘርዓይ ገብረስላሴ ሳጥን ውስጥ ያገኛትን ያለቀላት አጋጣሚ በአሊዮንዚ ናፊያን ከተመለሰበት በኋላ ብዙም ከእንቅስቃሴ ውጪ በሙከራዎች ያልደመቀው ጨዋታው 0ለ0 ተቋጭቷል።