ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና አቻ ተለያይተዋል

በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች የተቆጠሩ ግቦች ለሲዳማ ቡና እና ለሀዲያ ሆሳዕና አንድ አንድ ነጥብ አጋርተዋል።

ሲዳማ ቡና በሁለተኛ ዙር መጀመሪያ ጨዋታ ላይ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ነጥብ ተጋርተው ሲወጡ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አስቻለው ሙሴን በደግፌ አለሙ ተክተው ሲገቡ ሀዲያ ሆሳዕና በበኩላቸው ከሀዋሳ ከተማ 0ለ0 ሲለያዩ ከተጠቀሙት ቋሚ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ቃለአብ ውብሸትን በበረከት ወልደዮሐንስ፣ በየነ ባንጃን በዳግም ንጉሤ ተክተው ገብተዋል።

ሁለቱ ሁለተኛውን ዙር ነጥብ በመጋራት የጀመሩ ቡድኖችን ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን የምሽቱ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች በተደረጉ የወደፊት ሩጫዎች ግቦችን አስመልክቶናል።

በመጀመሪያ ፊሽካ ኳስ ተጀምሮ ሀዲያ ሆሳዕና ወደፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ኳስ ቀምተው በፈጣን ሽግሽግ አራተኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ በቅብብል ኳስ ይዘው ወደፊት ሲሄዱ ኳሷ ሀብታሙ ታደሰ እግር ስር ገብታ መሬት ለመሬት ሳጥን ውስጥ ለነበረው መስፍን ታፈሰ አቃብሎት ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎ ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓቸዋል።

ባልጠበቁት መንገድ ግብ ያስተናገዱት ከቤራዎቹ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት በቁጥር በርከት ብለው ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል በመድረስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሁለት ደቂቃ ብቻ ፈጅቶባቸዋል። 5ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ተመስገን ብርሃኑ የሲዳማ ቡናን ተከላካዮች አታሎ በማለፍ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ ሲያሻገር ኢዮብ ዓለማየሁ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው ጋርዶበት ድጋሚ ኳሷን አግኝቶ በግሩም ሁኔታ በተረከዙ መጥቶ ወደግብነት ቀይሮ አቻ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ከግቦቹ መቆጠር በኋላ የጥንቃቄ ጨዋታ ምርጫቸው ያደረጉት ቡድኖቹ እየተፈራረቁ የኳስ ቅብብል ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ግብ ለማስቆጠር የሚደርጉት ግስጋሴ በሚቆራረጡ ኳሶች ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ሲቸገሩ ለመመልከት ችለናል። በዚህም 17ኛው ደቂቃ ላይ ለሲዳማ ቡናዎች መስፍን ታፈሰ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ጠንከር ያለ ሙከራ አድርጎ የግቡ ዘብ ያገደበት እና ለሀዲያ ሆሳዕናዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ተሻምቶ ብሩክ በየነን ቀይሮ ሜዳ የገባው ደስታ ዋሚሾ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ቶማስ ኢካራ በቀላሉ ከተቆጣጠረባቸው ግልፅ ከሆኑ ከሁለት ሙከራዎች ውጪ ጠንከር ያለ የጠራ ሙከራ በአጋማሹ ሳንመለከት ቀርተናል። 24ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ብሩክ በየነ ጉዳት አስተናግዶ በአስገዳጅ ቅያሪ ደስታ ዋሚሾ ቀይሮ ሜዳ የገባበት ክስተት ተጠቃሽ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ተመልሶ በጥሩ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ እያንሸራሸሩ ለተመልካች ጥሩ የአንድ ለአንድ ቅብብል ቢያስመለከቱም አጨዋወታቸው ከቅብብል የዘለለ ከግብ ማግባት ሙከራዎች ጋር ግን መታጀብ ሳይችል ቀርቷል። ሆኖም ግን ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት በመሄድ ረግድ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ብልጫ የነበራቸው ሲሆን በተደጋጋሚ በቅብብል እንዲሁም በቆመ ኳስ የሲዳማ ቡናዎችን ተከላካይ መስመር የፈተኑ ኳሶችን ግብ ክልል ይዘው ሲገቡ ተመልክተናል።

ሲዳማ ቡናዎችም በአንጻራዊነት በፈጣን ሽግግር ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አምርቷል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከአንድ ነጥብ ይልቅ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ሁለቱም ቡድኖች ወደ ፊት የመሄድ እንቅስቃሴዎችን አጠናክረው ጠንካራ ባይሆኑም በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ሰንዘርዋል።

ይሁን እንጂ በኳስ ቅብብል ደምቆ በሙከራዎች ጋር መታጀብ ያልቻለው  የምሽቱ ጨዋታ ተጨማሪ ግብ የሚያስመለክተን ቢመስልም በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ውጪ ሌላ ግብ ሳያስተናገድ 1ለ1 ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።