ሪፖርት | ሐይቆቹ ምዓም አናብስቶቹን ረምርመዋል

ሪፖርት | ሐይቆቹ ምዓም አናብስቶቹን ረምርመዋል

ሰባት ጎሎች እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ባስመለከተን ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ግቦችን አስተናግደው ተሸንፈዋል።


መቐለዎች በንግድ ባንክ ካስተናገዱት ሽንፈት የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን በብሩክ ሙሉጌታ ፣ ቦና ዓሊን በያሬድ ከበደ ሲለውጡ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያለ ጎል አቻ ተለያይተው የነበሩት ሀዋሳዎች በበኩላቸው አቤኔዘር ዮሐንስን በቢኒያም በላይ በብቸኝነት ያደረጉት ቅያሪያቸው ሆኗል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ መቐለ 70 እንደርታዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ ሰይድ ሀብታሙ በሳጥን ውስጥ ብሩክ ሙሉጌታ ላይ በሰራው ጥፋት የዕለቱ ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ሰይድ ያሬድ ብርሀኑ የመታውን ኳስ በማዳን ሀዋሳን ከተመሪነት መታደግ ሲችል የተመለሰችውን ኳስ በድጋሚ ያገኘው ያሬድ ብርሀኑ ሌላኛዋን አጋጣሚ ዳግም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ዓሊ ሱለይማንን ይፈልጉ የነበሩ ኳሶችን ከተከላካይ ጀርባ የተንቀሳቀሱት ሐይቆቹ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል ፤ ዓሊ በረጅሙ ወደ ቀኝ የተጣለለትን ኳስ ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ ሁለቱን የመሐል ተከላካዮች ጭምር አልፎ በግሩም አጨራረስ ነበር ግቧን ያስቆጠረው።

ጨዋታው ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች እየቀሩም ሀዋሳዎች በዓሊ አማካኝነት ተጨማሪ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ማግኘት ቢችሉም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ለመቐለ ተከላካዮች ፋታ በሌለው እንቅስቃሴያቸው ጫና ያሳደሩት ሀዋሳዎች በጎል መድመቅ የጀመሩት ገና በማለዳው ነበር ፤ 50ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ባደረጋት ሙከራ መልስ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በደንብ መጠጋት የጀመሩት ሐይቆቹ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ከግራ ሳጥን ውስጥ እስራኤል አመቻችቾ የሰጠውን ኳስ ቢኒያም በላይ ወደ ግብነት ለውጧታል።

በሽግግር አጨዋወትም ይሁን ዓሊን በሚፈልጉ ረጃጅም ኳሶች ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ መጓዛቸው የቀጠሉት ሐይቆቹ 70ኛው ደቂቃ ከግራ አሸናፊ ሀፍቱ የተሳሳተውን ኳስ ያገኘው ብሩክ ታደለ በረጅሙ ጥሎለት ዓሊ በድንቅ አጨራረስ ሦስተኛ ጎል አድርጓታል።

የሀዋሳን ከፍ ያለ ማጥቃትን መቋቋም የከበዳቸው ሞዓም አናብስቱ በ82ኛው ደቂቃ ከተባረክ እና ብሩክ ንክኪ በኋላ ከሳጥን ጠርዝ ኳስን ያገኘው አቤኔዘር ዮሐንስ አራተኛ ጎልን እጅግ ግሩም በሆነ ምት ሶፎኒያስ መረብ ላይ አስቀምጦ የሀዋሳን መሪነት አሳድጓል።

አራት ጎሎችን ውጤቱን ለማጥበብ የሞከሩት መቐለዎች ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ያሬድ ብርሀኑ ሲያስቆጥራት 91ኛው ደቂቃ በተቃራኒው ሀዋሳዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ዓሊ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።


ጨዋታው ወደ ጭማሪ ደቂቃ ማምራቱን ተከትሎ ሀዋሳዎች በ93ኛው ደቂቃ ዓሊ ከቸርነት በረጅሙ ያገኘውን ኳስ በድንቅ አጨራረስ ለሀዋሳ አምስተኛ ለራሱ ደግሞ ሦስተኛ ጎል በማድረግ ሀትሪክ ሲሰራ 95ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቦና ዓሊ ለመቐለ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የሰባት ጎሎች ድራማ በመጨረሻም በሀዋሳ የ5ለ2 አሸናፊነት ተቋጭቷል።