አርባምንጭ ከተማዎች ከመመራት ተነስተው በአህመድ ሁሴን ሦስት ግቦች ታግዘው አዳማ ከተማን 3-1 ማሸነፍ ችለዋል።
(በኢዮብ ሰንደቁ)
ባሳለፍነው ሳምንት አዳማ ከተማዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 ከረቱበት ጨዋታ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ በተቃራኒ አርባምንጭ ከተማዎች ታምራት እያሱ እና በፍቅር ግዛውን በማሳረፍ አህመድ ሁሴን እና ፍቃዱ መኮንን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ሲል በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ስታድየም ከድል የተመለሱትን ሁለቱን ቡድኖች ባገናኘው ጨዋታ ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አዳማዎች የመጀመሪያ ግባቸውን ለማስቆጠር አንድ ደቂቃ ብቻ በቂያቸው ነበር።
ነቢል ኑሪ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ግብነት በመቀየር አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡም መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ተቀራራቢ የሆነ የኳስ ቁጥጥር ቢኖርም የአቻነቷን ግብ ለማግኘት በቁጥር በዛ ብለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት አዞዎቹ 25ኛው ደቂቃ ላይ አካሉ አትሞ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ አህብዋ ብሪያን በደረቱ አመቻችቶ ቢያቀብለውም ቡታቃ ሸመና የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ናትናኤል መልሶበታል። በድጋሚ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ አህብዋ ለአህመድ በግንባሩ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል ይህም ለአርባምንጮች ሌላኛው አስቆጪ ሙከራ ነበር። አዳማ ከተማዎችም ካስቆጠሩት ግብ ውጪ ምንም አይነት ዒላማውን የጠበቀ ኳስ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መሻሻልን አሳይተው የገቡት እና የኳስ ብልጫ በመውሰድ በቁጥር በዛ ብለው የተጋጣሚን የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመጎብኘት የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የነበሩት አርባምንጮች ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ 50ኛው ደቂቃ ላይ ቡታቃ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ አህመድ ሁሴን በድንቅ አጨራረስ በማስቆጠር አዞዎቹን አቻ አድርጓል።
ከአቻነት ግቡ በኋላ ይበልጥ ጫና ፈጥረው በመጫወት መሪ ለመሆን ሲሞክሩ የነበሩት አርባምንጮች 57ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት በመቀየር አዞዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
አዳማ ከተማዎች የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቻቸውን ሬድዋን ሸሪፍ በቀይ ካርድ ከሜዳ ማጣታቸውን ተከትሎ 30 ያክል ደቂቃዎችን በጎዶሎ ለመጫወት ተገደዋል።
በቁጥር ብልጫ መውሰዳቸው ይበልጥ አጥቅቶ ለመጫወት የተመቻቸው አርባምንጭ ከተማዎች በአህብዋ አማካኝነት በ70ኛው እና 74ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ያለቀላቸውን ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም በግብ ጠባቂው ናትናኤል አማካኝነት ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል። አጥቅተው መጫወታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አዞዎቹ የጨዋታው መደበኛው ሰዓት ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች ሲቀሩት ተቀይሮ የገባው ቻርለስ ከርቀት ለአህመድ ያሻገረለት ኳስ አህመድ በድንቅ አጨራረስ ወደ ለእሱም ለክለቡም ሶስተኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ይህንንም ተከትሎ አርባምንጭ ከተማዎች ከመመራት ተነስተው በአህመድ ሁሴን ሶስት ግቦች ታግዘው 3-1 ማሸነፍ ችለዋል።