አርባምንጭ ከተማ ኬኒያዊውን የቀድሞው ተከላካያቸውን ለማስፈረም ከጫፍ ሲደርሱ ከአጥቂያቸው ጋር ደግሞ በስምምነት ተለያይተዋል።
በሀያኛው ሳምንት ፋሲል ከነማን በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር በድል የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች ቡድናቸው ለማጠናከር ከቀናቶች በፊት ፀጋዬ አበራ እና ታምራት እያሱን ወደ ቡድናቸው መቀላቀላቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ የቀድሞው ተከላካያቸውን ለማስፈረም ከጫፍ መድረሳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ክለቡን ለመቀላቀል ከጫፍ የደረሰው ኬኒያዊው የመሐል ተከላካይ በርናንድ ኦቼንግ ነው ፤ ለአምስት ዓመታት ቪጋ እና ዋዚቶ ለተባሉ የሀገሩ ክለቦች ከተጫወተ በኋላ ከሁለት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በአርባምንጭ ከተማ መጫወት የቻለ ሲሆን ባሳለፍነው ዓመትም በሌላኛው የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ኢትዮጵያ መድን ቆይታ አድርጓል።
ያለፉትን ጊዜያት ክለብ አልባ ሆኖ የቆየው ኬንያዊው ተከላካይ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የቀድሞው ቡድኑ አርባምንጭን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ደግሞ በክረምቱ ከከፍተኛ ሊጉ ደሴ ከተማ አስፈርመውት ከነበረው አጥቂው ሙሉጌታ ካሳሁን ጋር እየገጠመው ካለው ተደጋጋሚ ጉዳት የተነሳ በስምምነት ስለ መለያየታቸውም አረጋግጠናል።