ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው አጋማሽ አብነት ደምሴ ባስቆጠራት ብቸኛ የግንባር ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 በመርታት ተከታታይ ሙሉ ነጥባቸውን አሳክተዋል።
በባህርዳር ከተማ አስደንጋጭ ሽንፈትን ካስተናገደው ቡድናቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ ባሕሩ ነጋሽ ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ ፣ ፍፁም ጥላሁን እና አብዱ ሳሚዮ በማስወጣት ተመስገን ዮሐንስ ፣ ቶሎሳ ንጉሴ ፣ አብዱላፊዝ ቶፊቅ እና አማኑኤል ኤርቦ በምትኩ ሲገቡ በኢትዮጵያ መድን ላይ ድል የተቀናጁት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ምንም ቅያሪን ሳያደርጉ ገብተዋል።
ሃያ ሁለተኛውን የሊግ ግንኙነታቸውን ምሽቱን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ በጥቅሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ አንድም ጥራት ያላቸውን አጋጣሚዎች ለመፍጠር ያልተሞከረበት ነበር። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደካማ እንቅስቃሴ አንፃር በተወሰነ መልኩ ረጃጅም የሆኑ ኳሶችን በመጠቀም ሦስተኛው ሜዳ በመድረስ የተሻለውን ጊዜ ያሳለፉት ወላይታ ድቻዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ አቅጣጫ ለመስመር ከተጠጋ ቦታ ቴዎድሮስ ታፈሠ ከቅጣት ምት ወደ ውስጥ አሻምቶ ፀጋዬ በጭንቅላት ጨርፎ የግቡ የግራ ቋሚ ብረትን ገጭታ ከተመለሰችዋ ኳስ በስተቀር በብዙ መልኩ ደካማ የነበረው እና በሙከራዎችም መድመቅ የተነሳው አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ የሁለት አጥቂዎችን ቅያሪ በማድረግ ፈረሰኞቹ ቢመለሱም በአጋማሹ ወደ ሳጥን የተጠጋውን እንቅስቃሴ በይበልጥ ያደረጉት ግን የጦና ንቦቹ ሆነዋል። ከራስ ሜዳ በሚነሱ ረጃጅም ወደ መስመር መዳረሻቸውን ባደረጉ እንዲሁም ከቆሙ ኳሶችም ጭምር በድግግሞሽ የተጋጣሚያቸው ሦስተኛ ሜዳ ላይ ይገኙ የነበሩት ድቻዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል።
ከግራው የሜዳ ክፍል ለመስመር ከተጠጋ ቦታ ላይ ተደጋጋሚ ቅጣት ምቶችን በጨዋታው ሲያደርግ የነበረው ቴዎድሮስ ታፈሠ ያሻማውን ኳስ አብነት ደምሴ በግንባር በመግጨት ተመስገን ዮሐንስ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አድርጓል። በመፈራረቅ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ለመያዝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንጂ ዕድሎች በበቂ ሁኔታ ያልታዩበት ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ ወደ መጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች መጠነኛ መነቃቃትን ቢያሳዩን ፍፁም ጥላሁን እና ቢኒያም ፍቅሬ ከሰነዘሯቸው ሁለት ደካማ ሙከራዎች ውጪ የወላይታ ድቻን የኋላ አጥር ማስከፈቱ ከብዷቸው ታይቷል።
መጠነኛ የኃይል አጨዋወትን እያስተዋልንበት 82ኛው ደቂቃ ጨዋታው ሲደርስ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት ቴዎድሮስ ታፈሠ ያለቀለት አጋጣሚን አግኝቶ ካመከናት በኋላ ጨዋታው በመጨረሻም በጦና ንቦቹ የ1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።