ቢጫዎቹ ቡድናቸውን ማጠናከር ቀጥለውበታል

ቢጫዎቹ ቡድናቸውን ማጠናከር ቀጥለውበታል

ወልዋሎ ናይጀርያዊውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል።

በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙት እና ቀደም ብለው ሳሙኤል ዮሐንስ፣ ሀብታሙ ንጉሤ፣ ፉዓድ አዚዝ እና ሙሳ ራማታህን የግላቸው ያደረጉት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ናይጄርያዊውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል። ቡድኑ ለመቀላቀል ከስምምነት የደረሰው ተጫዋች ደግሞ ከወራት በፊት ከሱዳኑ አል ሜሪክ በስምምነት የተለያየው የሃያ ዘጠኝ ዓመቱ ኦሎሩንሌኬ ኦጆ ነው።

ክለቡን በአምበልነት እየመራ የሀገሪቱ ሊግ ዋንጫ ያነሳበትን ኢንየምባ ጨምሮ በካኖ ፒላርስ፣ ሰንሻይን ስታርስ፣ አክዋ ዩናይትድ እና አቢያ ዋሪርስ እና አል ሜሪክ መጫወት የቻለው ባለልምዱ ግብ ጠባቂ ከሱዳኑ  አልሜሪክ በስምምነት ከተለያየ በኋላ መዳረሻው ወልዋሎ ዓ.ዩ ሆኗል። በ2015 በተካሄደው ከሀያ ዓመት አፍሪካ ዋንጫ ከናይጀርያ ጋር የውድድሩ አሸናፊ የነበረው ግብ ጠባቂው  በ2023 በኮትዴቭዋር አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫም ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አባል ነበር።

በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ የገባው ግብ ጠባቂው በዛሬው ዕለት የህክምና ምርመራውን አጠናቆ በቀጣይ ቀናት ፌርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።