ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የ22ኛው ሳምንት በወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ የሚገኙት ሐይቆቹ እና መሪውን እግር በእግር በመከታተል ላይ የሚገኙት ቡናማዎቹ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል።

ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ በጥሩ መነቃቃት ያላቸው ሀዋሳ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ መቐለን አምስት ለሁለት በማሸነፍ ነጥባቸውን አስራ ዘጠኝ አድርሰው ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ካሉት ክለቦች ጋር ያላቸውን ልዩነት ቀንሰዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረትን ከቀጠሩ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች የሰበሰቡት ሐይቆቹ በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ያሳዩት ብቃት አሁንም ወደ ተቃናው መንገድ ለመመለስ ሩቅ ስላለመሆናቸው ማሳያ ሊሆን ይችላል። የሚፈጥሯቸውን ዕድሎች ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ መሻሻሎችን ያሳዩት ሀዋሳዎች ከዚህ ቀደም በአስራ ሦስት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት የግብ መጠን በአንድ ጨዋታ ማስቆጠር ችለዋል፤ በቀጣይም  መወገድ የሚችሉ የመከላከል ስህተቶችን መቀነስ ከቻሉ አሁንም ቢሆን ካሉበት ስፍራ ቀና ማለታቸው የሚቀር አይመስልም።

ሆኖም በነገው ዕለት በሊጉ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ከሚገኙ ክለቦች አንዱ የሆነው እና በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በማድረግ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርበው ቡና እንደመግጠማቸው ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።

በሰላሣ ሁለት ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እና በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገው በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች የአሸናፊነት መንገዳቸውን ለማስቀጠል በወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ ከቆመው ሀዋሳ ከተማ ጋር ይፋለማሉ።

ሰላሣ ሁለት ነጥቦች ሰብስበው ከመሪው በስድስት ነጥቦች ልዩነት  ላይ የሚገኙት ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታ የሚያገኙት ነጥብ የተለየ የደረጃ መሻሻልን ሊያመጣላቸው ባይችል እንኳን ወደ መሪው ለመቅረብ ወይም ጫና ለማሳደር የሚያግዛቸው ነው።

ቡናማዎቹ በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገደው መድን በመቀጠል ጥቂት ግቦች ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ገንብተዋል፤ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መረቡን አስከብሮ የወጣው ቡድኑ ድል ባደረገባቸው ጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር አለመቻሉ የሚያሳስበው ጉዳይ ይመስላል። ቡድኑን ከተቀላቀሉበት የባለፈው ውድድር ዓመት ጀምሮ ለመከላከል አደረጃጀቱ እና ከኳስ ውጭ ላለው እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ አቀራረብ ያላቸው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በቀጣይ የቡድናቸው የግብ ማስቆጠር አቅም ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ስድስት ድል፣ አንድ ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤቶች ባስመዘገበባቸው ያለፉት አስር የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ በውጤት የታጀበ ጥሩ ብቃት ማሳየት ቢችልም በአንድ ጨዋታ ብቻ ከአንድ ግን በላይ ማስቆጠሩም የአፈፃፀም ብቃቱን ከፍ ማድረግ እንዳለበት ማሳያ ነው።

ከሊጉ የተሳትፎ ዝርዝር ጠፍተው የማያውቁት ክለቦቹ ከዚህ ቀደም ለ51 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና 18 ጊዜ ድል ሲያደርጉ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች 16 ድል አድርገዋል የተቀሩት 17 ግንኙነቶች ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተደመደሙ ነበሩ። ኢትዮጵያ ቡና 64 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 55 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።