ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ ግልፅ የግብ ዕድሎችን ሳያስመለክተን 0ለ0 ተቋጭቷል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ መቐለን ቡና ደግሞ ኤሌክትሪክን በረቱበት ወቅት የተጠቀሙትን አሰላለፍ በተመሳሳይ ሁለቱም ቡድኖች ለውጥን ሳያደርጉ ለዛሬው ጨዋታ ይዘው ገብተዋል።
በኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው የተመራው የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የተመጣጠነ እንቅስቃሴን ቡድኖቹ ቢያደርጉም እንደነበረው ከፍ ያለ ግለት ግን ጥራት ያላቸውን አጋጣሚዎች ያላየንበት ነበር።
ጨዋታው እንደተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ ፈጥነው በቅብብል የሀዋሳ ሜዳ ላይ የተገኙት ቡናማዎቹ አማኑኤል ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻግር ወንድማገኝ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ለጥቂት በራሱ ላይ ለማስቆጠር በተቃረበበት ፈጣን ሙከራን አድርገዋል።
እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ኳስን ከተቆጣጠሩ በኋላ ዓሊን የሚፈልጉ ኳሶችን የማጥቂያ መነሻ ያደርጉ የነበሩት ሐይቆቹ 14ኛው ደቂቃ ዓሊ ከግራ ይዞ የገባውን ኳስ ተባረክ ሞክሮ በግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ርብርብ የወጣበት እና ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታትን ዳላንድ ኢብራሂም ያመከነበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ዕድሎች ነበሩ።
በይበልጥ በመፈራረቅ የጨዋታ ብልጫውን ለመውሰድ ከሚደረጉ የሜዳ ውስጥ ፉክክር ውጪ በሙከራዎች መድመቅ የተሳነው አጋማሽ ቡናማዎቹ 28ኛው ደቂቃ ከይታገሱ ታሪኩ መነሻ የሆነችን ኳስ ዲቫይን ከሳጥን ውጪ መቶ ሰይድ ከተቆጣጠራት ሙከራ በኋላ አጋማሹ ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል ለማምራት ተገዷል።
እንደ መጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛውም አጋማሽ ሜዳ ላይ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች በስተቀር የጎል ሙከራዎችን ማስናፈቁን የቀጠለው ጨዋታ ተመሳሳይ የሆነን የኳስ ቁጥጥር ሁለቱም በመጠቀም በተደጋጋሚ በፍጥነት የመጨረሻው ሜዳ ላይ የተገኙበት ቢሆንም የጎል ዕድሎችን ግን የፈጠሩበት አልነበረም።
59ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ተፈራ ለቡናማዎቹ ጎል ቢያስቆጥርም በሂደቱ በሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሰይድ ሀብታሙ ላይ ጥፋት ሰርተሀል በሚል ከተሸራው ኳስ ውጪ ሀዋሳ ከተማም ይሁን ኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ውስጥ በድግግሞሽ ደርሰው መመልከት ቢቻልም የሚገኙ አጋጣሚዎች መጠቀም ባለ መቻላቸው ጨዋታው በመጨረሻም ያለ ጎል ሊደመደም ችሏል።