ባህር ዳር ከተማዎች በፍቅረሚካኤል ዓለሙ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን 1ለዐ በመርታት ከመሪው ያላቸውን ርቀት ማጥበብ ችለዋል።
በኢዮብ ሰንደቁ
ሀዲያ ሆሳዕናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከ ሲዳማ ቡና ጋር 1-1 ከተለያዩበት አሰላለፍ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ብሩክ በየነን በማሳረፍ በምትካቸው በየነ ባንጃ እና ከማል ሀጂን በማስገባት ሲጀምሩ በተቃራኒው ባህር ዳሮች ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ቋሚ አሰላለፍ ላይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ አምሳሉ ጥላሁንን በግርማ ዲሳሳ በመቀየር ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
9 ሰዓት ሲል በተጀመረው ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህርዳር ከተማን ባገናኘው የዕለቱ መርሐግብር የመጀመሪያ ጨዋታ ከጅማሮው አንስቶ ጥሩ የሆነ የኳስ እንቅሰቃሴዎችን ያስመለከተን ጨዋታ ነበር። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ፊት ሂዶ የማጥቃት ፍላጎት የነበረ ቢሆንም ግን ይሄ ነው የሚባል ጥሩ የኳስ ሙከራ ሳያስመለክተን ቆይቷል።
በአጋማሹ መጀመሪያ እና መጨረሻ ጀቂቃዎች ላይ ተጋጣሚ ላይ ጫና በማሳደሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የባህር ዳር ተከላካዮችን አጥር ማፍረስ ተስኗቸዋል። በተቃራኒ መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው የነበሩት ባህር ዳሮች በ40ኛው ደቂቃ ፍፁም አለሙ ከርቀት ከሞከረው ደከም ያለ ሙከራ በስተቀር በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም ዓይነት ሙከራ ሳያስመለክተን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መሻሻሎችን በማድረግ ወደ ሜዳ የተመለሱት ባህር ዳር ከተማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ መልኩ የተጋጣሚን ግብ መጎብኘት የቻሉ ሲሆን በፍሬው ሰለሞን ቀይረው ያስገቡት ፊሊፕ ለማጥቃት መሰረት የሆኑ ኳሶች ከእርሱ በመነሳት ለቡድኑ ቁልፍ የሆነ ሚና ሲያበረክት ተስተውሏል።
በቁጥር ብልጫ በመውሰድ ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ባህር ዳር ከተማዎች 62ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመጠጋት ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ መትቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ለጥቂት ወጥቶበታል።
የመደበኛ ሰዓቱ ተጠናቆ 4ኛው ዳኛ ጭማሪ ደቂቃዎችን ለማሳየት በተዘጋጁበት ሰዓት ባህር ዳር ከተማዎች ከቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት መሳይ ሲያሻማ እሱ ያሻማውን ኳስ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ለቡድኑ የጭንቅ ሰዐት ደራሽ መሆን ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ባህር ዳር ከተማዎች ወሳኝ ድልን መጎናፀፍ ችለዋል።