ሪፖርት | ጥሩ ፉክክር የነበረው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

ሪፖርት | ጥሩ ፉክክር የነበረው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

የሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 0ለ0 ተፈፅሟል።

ሲዳማ ቡና ከሀድያ ሆሳዕናው የ1ለ1 ውጤት በሦስት ቋሚዎቻቸው ላይ ለውጥን ሲያደርጉ ደግፌ ዓለሙን በአስቻለው ሙሴ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን በማይክል ኪፕሩቪ ፣ መስፍን ታፈሠን በአበባየሁ ሀጂሶ ሲተኩ በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት አዳማዎችም በኩልም በተመሳሳይ በሦስቱ ላይ ባደረጉት ቅያሪ ፍቅሩ አለማየሁ ፣ ስንታየሁ መንግስቱ እና ሬድዋን ሸሪፍ ወጥተው መላኩ ኤልያስ ፣ ፉዓድ ኢብራሂም እና ቢኒያም ዐይተን ተክተዋቸው ገብተዋል።

መጠነኛ ፉክክርን ከመነሻው አንስቶ እያሳየን የተጓዘው ጨዋታ በንፅፅር ሲዳማ ቡና በሽግግር እና ከቆሙ ኳሶች ሦስተኛው ሜዳ ላይ በመድረስ የተሻሉ ሆነው የተገኙበት ቢሆንም የመጨረሻ ውሳኔያቸው ግን ስልነት የጎደለው ነበር። 6ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከቀኝ የተገኘን የቅጣት ምት ወደ ውስጥ አሻምቶ አበባየሁ ሀጂሶ በቀላሉ ለግብ ዘቡ ናትናኤል ተፈራ ያሳቀፈረበት አጋጣሚ በአጋማሹ በሲዳማ ቡና በአጋማሹ የተደረገች ጠጣሯ ሙከራ ነበረች።

ቢኒያም እና ነቢል በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የሚያገኟቸውን ኳሶች ለመጠቀም ያደርጉት ከነበረው ግላዊ ጥረቶች ውጪ በብዙ ረገድ ተዳክመው የቀረቡት አዳማዎች 17ኛው ደቂቃ ደቂቃ ላይ አበባየሁ ለሲዳማ ካደረጋት ደካማ ሙከራ መልስ በብዙ መመዘኛ የደበዘዘው አጋማሽ ያለ ጎል ተጋምሷል።

ከዕረፍት ከቆመበት ደካማ እንቅስቃሴ የቀጠለው ጨዋታ ከመጀመሪያው አኳያ በአንፃራዊነት ተመጣጣኝ ፉክክሮችን ማስተዋል የቻልንበት ይሁን እንጂ ጥራት ባለው ሙከራ ግን መታጀብ አልቻለም። መጠነኛ የሐይል አጨዋወቶች የተበራከቱበት አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ረዘም ባሉ የሽግግር አጨዋወት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በአንድ ሁለት ቅብብል በተለይ የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ብልጫውን ወስደው በድግግሞሽ ሦስተኛው ሜዳ ላይ መገኘት የቻሉበት ቢመስልም በብዙ ረገድ ወረድ ያለ አቀራረብ የነበረው ጨዋታ በመጨረሻም ያለ ጎል ተጠናቋል።