የሊጉ መሪ መድን እና የውድድር ዓመቱ ጉዞውን ያቃናው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ መርሐግብር ነው።
በወላይታ ድቻ ሽንፈት በማስተናገድ ሁለተኛውን ዙር የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች በመጨረሻው መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማ ላይ የተቀዳጁትን ድል ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማሉ። ተከታዮቹ ኢትዮጵያ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን የሚያሰፉበት ወርቃማ ዕድል ያገኘው ቡድኑ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻለ ልዩነቱ ወደ ስምንት ከፍ የሚያደርግበት ወርቃማ ዕድል በእጁ ይገኛል። ከመጨረሻዎቹ ስድስት ድሎች ውስጥ በአምስቱ በጨዋታ ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር ያልቻለው ቡድኑ በቀዳሚነት የግብ ማስቆጠር አቅሙን ከፍ ማድረግ ይኖርበታል። ቡድኑ በነገው ዕለት ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ እና በጥሩ የመከላከል ብቃት ላይ ያለው ቡድን ስለሚገጥምም የማጥቃት አጨዋወቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ የአፈፃፀም ወደ ጨዋታው መቅረብ ይጠበቅበታል።
በውድድር ዓመቱ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ተመሳሳይ አቀራረብ ካለው ቡድን የሚገጥማቸው ፈተና በምን መንገድ ይወጡታል የሚለው ነገርም ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።
የመጀመርያ ዙር ደካማ ውጤቱን ቀልብሶ በተቃና የድል መንገድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሃያ ስምንት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የሊጉን መሪ በሚገጥምበት የነገው ጨዋታ ድል ማድረግ ከቻለም ደረጃውን የሚያሻሽልበት ዕድል አለ።
ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ሁለተኛው ዙር በጥሩ ብቃት የጀመሩት ንግድ ባንኮች ሽንፈት ሳይቀምሱ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ተጉዘዋል። ንግድ ባንክ በተለይም በቅርብ ሳምንታት እንደ ቡድን ጥሩ መንቀሳቀሱ ባይካድም የኋላ ክፍሉ ጥንካሬ ግን ለቡድኑ መሻሻል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፤ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ መረቡን አስከብሮ አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው የመከላከል ጥምረቱ በነገው ዕለት የሚኖረው ብቃትም የጨዋታው ውጤት መወሰን ከሚችሉ ፍልሚያዎች አንዱ ነው።
ንግድ ባንክ ውድድሩ በሀገራዊ ጨዋታዎች ምክንያት ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ማሳካት ከቻለ ወደ ደረጃው ወገብ የመጠጋት ዕድል ያለው በመሆኑ በቀላሉ የሚመለከተው ጨዋታ አይሆንም፤ ይህ እንዲሆን ግን የወጥነት ችግር የሚስተዋልበት የፊት መስመር በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገደው ጠንካራው የመድን የመከላከል አደረጃጀት የሚጠብቀው ከባድ ፈተና በድል መወጣት ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል ሚሊዮን ሰለሞን እና ረመዳን የሱፍ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካሉት ፉዓድ ፈረጃ እና ሱሌማን ሀሚድ በስተቀር ስብስቡ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ነው።
ክለቦቹ በታሪካቸው 23 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10 ፣ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 3 ጊዜ ሲያሸንፉ 10 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ንግድ ባንክ 37፣ መድን ደግሞ 23 ግቦችን አስቆጥረዋል።