ወደ ሊጉ አናት የመጠጋት ወርቃማ ዕድል ያገኙትን የጦና ንቦቹ እና በሊጉ ግርጌ የተቀመጡትን ቢጫዎቹ የሚያፋልመው ጨዋታ የነገ ሁለተኛ መርሐግብር ነው።
በሁለተኛው ዙር ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸውን ሰላሣ ያደረሱት ወላይታ ድቻዎች በ6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ጥሩ ብቃት የመጡት የጦና ንቦቹ ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን ማሳካት ችለዋል፤ በ2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተከታትለው ከተቀመጡት ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር በነጥብ የሚስተካከሉበት ዕድል በእጃቸው ይዘው ወደ ጨዋታው የሚቀርቡት የጦና ንቦቹ በተለመደው ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ያተኮረው አጨዋወት እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል። በውድድር ዓመቱ ሃያ አንድ ግቦች አስቆጥሮ በተመሳሳይ ሃያ አንድ ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በመከላከሉ ረገድ ጥሩ መሻሻሎች አሳይቷል፤ በድምሩ አራት ግቦች አስተናግዶ ከተሸነፈባቸው ሁለት ጨዋታዎች በኋላ በተከናወኑ አራት መርሐግብሮች አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ አወንታዊ ለውጥ ማምጣት ቢችልም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያለው ብቃት ግን ከዚህም በላይ መሻሻል የሚገባው ጉዳይ ነው።
ቡድኑ በነገው ዕለት ድል የሚቀናው ከሆነ ከአስር የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከ5ኛ በላይ ባሉ ደረጃዎች መቀመጥ ይችላል፤ ይህንን ተከትሎም ከወትሮው በተለየ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ወደ ጨዋታው ይገባል ተብሎ ይገመታል።
በዘጠኝ ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች የውድድር ዓመቱ አካሄዳቸውን ለማስተካከል ይፋለማሉ።
ወልዋሎ ዘግይቶም ቢሆን ከውድድር ዓመቱ ደካማ ብቃት አንሰራርቷል፤ ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ነጥብ ማስመዝገብ የጀመረው ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ሽንፈት ብቻ በመቅመስ ቢያንስ ከተከታታይ ሽንፈቶች ርቋል። ሆኖም ቡድኑ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች አለመላቀቁ እና በሊጉ ከአንድ ድል በላይ ማስመዝገብ የመቸገሩ ጉዳይ ዋነኛው ፈተናው ሆኗል። ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች በአምስቱ ነጥብ ተጋርተው መውጣት የቻሉት ቢጫዎቹ በቀጣይ መቻልን በገጠመበት የመጨረሻ የሊግ ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሶ ከአራት መርሐግብሮች በኋላ ግብ ሳያስተናግድ መውጣት የቻለው የመከላከል ጥምረት ጥንካሬ ማጎልበት ይኖርባቸዋል። በዝውውር መስኮቱ ስድስት ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉት ወልዋሎዎች ከውጭ ያስፈረሟቸው ፉሀድ አዚዝ፣ ሙሳ ራማታህ፣ ናይጀርያዊውን ግብ ጠባቂ ኦሎሩንሌኬ ኦጆ እና መናፍ ዑመር የወረቀት ጉዳዮች ባለማጠናቀቃቸው በነገው ጨዋታ አይሳተፉም።
በወላይታ ድቻ በኩል ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ከመሆኑ በስተቀር ሌላ የጉዳትም ሆነ የቅጣትም ዜና የለም። በወልዋሎ በኩልም ዮናስ ገረመው በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። አዲስ ፈራሚው ሳሙኤል ዮሐንስም በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።
የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 5 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 1 ጊዜ ድል ሲቀናው በተቀሩት 4 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፤ የጦና ንቦቹ አምስት ግቦች ሲያስቆጥሩ ቢጫዎቹ ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል።