ኢትዮጵያ መድን ንግድ ባንክን 2ለ1 በማሸነፍ በሰንጠረዡ አናት የስምንት ነጥብ ልዩነት ከፈጠሩበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን
ስለ ተከታታይ ድሎች..
“እንደየ ተጋጣሚያችን የተለያየ ነው ፐርፎርም ያደረግነው። በእርግጥ የዛሬው ጫናው በጣም ከባድ ነው። አንደኛ ንግድ ባንክ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው። ስብስቡም ጥሩ ነው ለእኛ የሚኖራቸውን አቀራረብም እናውቀዋለን እና ከባድ ጨዋታ ነበር። ካለፉት ጊዜያቶች ሁሉ በተለየ ሁኔታ ዛሬ ጫናው ብዙ ነው። የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል እኛ መሪ ስለሆንን ያንን ለማስጠበቅ ጋፑን አስፍተን ለመጠበቅ ከመፈለግ አንጻር ውጤቱ ያስፈልገን ነበር። እነሱም እንደዚሁ የመጡበት ሁኔታ ጥሩ ስለነበር በጣም ከባድ የሆነ ጨዋታ ነበር። እንደ አጠቃላይ ግን እኛ የምንፈልገውን ነገር አግኝተናል። አሁን ወደ ዕረፍት ሲሄዱ ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል።
በደረጃው አናት የሚገኙ ክለቦች ነጥብ መጣል እና ልዩነቱ ወደ ስምንት ከፍ ማለቱን ተከትሎ የዛሬው ውጤት ምን ዓይነት ትርጉም ይኖረዋል…?
“ገና 14 ጨዋታ ይቀራል ስለዚህ ስምንት ነጥብ ይሄን ያህል ዋስትና ይሰጣል ማለት አይደለም ከባድ ነው። በእግርኳስ ውስጥ የማያጋጥም ነገር የለም። ከዚህ በኋላ በጥንቃቄ መጎዝ እንፈልጋለን ለእኛ ጥሩ ማነቃቂያ ነው። ተነሳሽነታንን ይጨምራል ፣ ወደፊት እንድንሄድም ያደርገናል እንጂ ሊያስኮፍሰን ወይም በራስ መተማመን ብዙ ሊጨምርልን አይችልም። ይሄ ለልጆቼ የምነግራቸው ነው 14 ጨዋታ ማለት በጣም ብዙ ነው። እንደ ውጤት ግን አሁን ባለበት ደረጃ ጥሩ ነገር ነው።
ስለዚህ አሁን ላይ ኢትዮጵያ መድን ለዋንጫ ነው የሚጫወተው ብንል ስህተት ይሆናል?
“ላይሆን ይችላል ግን ያህል አስፍተነዋል ማለት አይቻልም እንዳልኩት በእግርኳስ የሦስት ጨዋታ ነጥብ ማለት ነው። ይሄ ደግሞ ለምሳሌ ባለፈው ሀዲያ ተከታታይ ስድስት አሸንፎ ከአራት ነጥብ የት እንደደረሰ ዐይተናል እና አይታወቅም። ምክንያቱም ብዙ ነገሮች ታሳቢ እያደረግክ ነው የምትጫወተው አንደኛ ሜዳ አለ መተዋወቅ አለብህ። የትም ቢሄድ ሊያጋጥም የሚችል ፈተና ይኖራል እና እነዚህን ተጋፍጠህ ነው የምትወዳደረው እና አሁንም ቢሆን ሌላ ዋስትና የሚሰጥ አይደለም።
አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ስለ ጨዋታው…
“ጨዋታው በብዙ መልኩ ጥሩ ነበር ብዬ አስባለሁ። በፍላጎት ነበር የተጫወትነው የ9 ሰዓት ጨዋታ አይመስልም ፤ አየሩ ስለሚከብድ ብዙም እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ አታይም። ጠንካራ ጨዋታ ነበር እነሱ መሪነታቸውን ለማጠናከር እኛ ደግሞ ልዩነቱን ለማጥበብ የነበረው ሽኩቻ እና የመሸናነፍ ስሜት ጥሩ ነበር። በብዙ የእግርኳስ መስፈርቶች ጥሩ ነበርን ግን ዕድለኛ አልነበርንም። መጨረሻ ላይ ያው ተሸንፈናል የእግርኳስ ባሕርይ ነው።”
ጎሎቹ ስለተቆጠሩበት መንገድ…
“የመጀመሪያው ጎል ስህተት አትለውም ይሄ እግርኳስ ውስጥ ያለ ነገር ነው። ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ድንገት የተፈጠረ ነገር ነው። ከዚያ ወደ ጨዋታው ቅኝት መመለስ ችለን ነበር እንደገና ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ነው የገባብን ያ ትኩረት ማነስ ይመስለኛል። ንፋሱም አለ በተጨማሪም የራሳችንም ስህተት አለ እና ያጋጥማል።”
አጠቃላይ የአዳማ ቆይታችሁ…?
“በአጠቃላይ መጥፎ አይደለም የአዳማ ቆይታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቡድኑ እየተስተካከለ ፣ በመካከል የተጎዱ ልጆች እየተመለሱ ነበር። ከሁሉም በላይ የነበረው ማሸነፍ ስሜት ለቡድኑ መስተካከል ማሳያ ነው።”
በቀጣይ ለማስተካከል የሚደረጉ ጥረቶች…?
“ባለው ዕረፍት ደካማ ጎናችንን እያስተካከልን ለመምጣት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።”