እጅግ ጠንካራ ፉክክር የተመለከትንበት የወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጨዋታ በካርሎስ ዳምጠው ብቸኛ ግብ ድቻዎችን 1ለ0 አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል።
ድቻዎች ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ድላቸው መልካሙ ቦጋለ እና ውብሸት ክፍሌን በአዛሪያስ አቤል እና ናትናኤል ናሲሩ ሲተኩ ከመቻል ጋር ነጥብ ተጋርተው የነበሩት ወልዋሎች በበኩላቸው ሳሙኤል ዮሐንስን በዳዊት ባህሩ ብቻ ለውጠው ቀርበዋል።
በፌድራል ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ እየተመራ የጀመረው የምሽቱ መርሃግብር ከአጀማመሩ አንስቶ ማራኪ ፉክክርን ሲያስመለክተን የነበረ ቢሆንም የተፈጠሩ አጋጣሚዎች ግን እጅግ ጥቂቶች ነበሩ።
ወላይታ ድቻዎች ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ አልያም ደግሞ ካርሎስ ዳምጠውን ባማከለ አጨዋወት ሲቀርቡ ወልዋሎዎች በበኩላቸው ደግሞ ወደ ዳዊት ባህሩ ወደ ተሰለፈበት የግራ መስመር ባደሉ ኳሶች በይበልጥ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ቢታይም የግብ ዕድሎች መፈጠር የጀመሩት ግን ከሰላሳ ደቂቃዎች በኋላ ነበር።
የጦና ንቦቹ 31ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ መዳረሻዋን ያደረገች ኳስን ፀጋዬ ብርሀኑ በጥሩ ዕይታ አቀብሎ ካርሎስ ዳምጠው በቀላሉ በረከት አማረ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ጎሏን ካስቆጠሩ በኋላ ከፍ ያለ መነቃቃት ያሳዩት ወላይታ ድቻዎች ወደ ሳጥን ተጠግተው ያሳዩ የነበሩት እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ሆነው መታየታቸው ዋጋ ሊያስከፍላቸው ቀርቦ ነበር።
በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በዳዊት ባህሩ ላይ ናትናኤል ናሲሩ ሳጥን ውስጥ በሰራው ጥፋት የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቲሳ ቢመታም ቢኒያም ገነቱ እና የግቡ ቋሚ ተጋግዘው አምክነውበታል።
በበርካታ መመዘኛዎች ማራኪ እንቅስቃሴዎችን ያስመለከተን የሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለመሸናነፍ ግለቱ ከፍ ያለን እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉበት ቢሆንም የመጨረሻው ሜዳ ላይ የነበራቸው ጥድፊያ እና አለመረጋጋቶች ግን የተገኙ ዕድሎች ወደ ጎልነት እንዳይለወጧቸው አድርጓቸዋል።
72ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው እና ሜዳ ላይ ከአንድ ደቂቃ ያነሰ ቆይታ የነበረው ናትናኤል ሠለሞን ከርቀት አደገኛ ሙከራን አድርጎ ቢኒያም ገነቱ ያከሸፈበት አጋጣሚ ቢጫዎቹ ያደረጓት ጠንካራ ሙከራቸው ነበረች።
ከተጋጣሚያቸው ቀላል የማይባል ፈተና ቢገጥማቸውም ያስቆጠሯትን ጎል አስጠብቆ ለመውጣት ከኋላ ሽፋን ከመስጠት ባለፈ በመልሶ ማጥቃት አደገኛ አካሄድ የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች 96ኛው ደቂቃ ላይ ሙከራ ሰንዝረዋል።
የወልዋሎው አዲሱ ፈራሚ ሙሳ ራማታ የመጨረሻ ኳስ ላይ ዘላለም አባተን በመጥለፉ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከተወገደ በኋላ የተገኘችዋን የቅጣት ምት አብነት ደምሴ መቶ በረከት አማረ ካዳናት ሙከራ በኋላ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።