የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ ከሆኑት መርሐ-ግብሮች ውስጥ ምዓም አናብስት እና አዞዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ረፋድ ላይ ይካሄዳል።
በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ከገጠማቸው መጠነኛ መንገራገጭ በኋላ በሁለተኛው ዙር የተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ የቻሉት አዞዎቹ ነጥባቸው ሰላሣ በማድረስ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በዘንድሮ የውድድር ዓመት ክስተት የሆነ የፊት መስመር ጥንካሬ ካላቸው ቡድኖች ከፊት የሚጠቀሱት አርባምንጭ ከተማዎች ከሊጉ መሪ በመቀጠል ከመቻል ጋር በጣምራ 2ኛ ከፍተኛ የግብ መጠን ማስመዝገብ ችለዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አስር ግቦች ያስቆጠረው በአሕመድ ሑሴን የሚመራው የፊት ጥምረት በነገው ጨዋታም ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሦስት መርሐ-ግብሮች ሰባት ግቦች አስተናግዶ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች መጠነኛ መሻሻሎች ያሳየው የመከላከል ጥምረቱም የቅርብ ሳምንታት በጎ ለውጡን ማስቀጠል ይኖርበታል።
በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት መቐለ 70 እንደርታዎች በሀያ ሁለት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በስጋት ቀጠናው ካሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው መቐለ ከአራት የጨዋታ ሳምንታት በፊት አዳማ ከተማ ላይ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ዳግም ለማሳካት እንዲሁም ከወራጅ ቀጠናው ስጋት የመላቀቅ ሀሳብ ሰንቆ ነገ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል። በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በጥሩ የመከላከል አቅም መረባቸውን ሳያስደፍሩ ከዘለቁ በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግቦች ማስተናገድ የጀመሩት ምዓም አናብስት ሀዋሳ ከተማን በገጠሙበት የመጨረሻ ጨዋታ ግን ይባስ ብሎ አምስት ግቦች ማስተናገድ ችለዋል።
ቡድኑ በጨዋታው የነበረው አጠቃላይ የመከላከል መዋቅር ዋጋ አስከፍሎታል። በዋናነት ደግሞ ወደ መሃል ተጠግተው በ’High line’ የተጫወቱት የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች እንቅስቃሴ የቡድኑን የኋላ መስመር አጋልጦታል፤ በጨዋታው ከተቆጠሩባቸው አምስት ግቦች ውስጥ ሦስቱ መነሻቸው ከተከላካይ ጀርባ የነበረው ሰፊ ክፍት ቦታ መሆኑም የድክመቱ ማሳያ ነው። ቡድኑ ቋሚ ተሰላፊዎቹ ቤንጃሚን ኮቴ እና መድሐኔ ብርሃኔ በቅጣት በማያሰልፍበት የነገው ጨዋታም ተጋጣሚው እንደ አሕመድ ሑሴን አይነት ታታሪ ተጫዋቾች የያዘ የፈጣን ሽግግር ቡድን እንደመሆኑ የተጠቀሰው ድክመት ቀርፎ መቅረብ ይኖርበታል። ቡድኑ ሁለት ተከላካዮቹ በቅጣት ማጣቱን ተከትሎ በአዲስ የመከላከል ጥምረት ጨዋታውን ይጀምራል ተብሎም ይጠበቃል።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል ከሳሙኤል አስፈሪ፣አበበ ጥላሁን እና አሸናፊ ተገኝ ጉዳት በተጨማሪ እንዳልካቸው መስፍን እና በፍቅር ግዛው በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን አሸናፊ ፊዳ አሁንም በቅጣት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል። ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው አዲሱ ፈራሚያቸው ኬኒያዊው የመሐል ተከላካይ በርናንድ ኦቼንግ የወረቀት ጉዳዮች ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ግን በጉዳት በርካታ ተጫዋቾች ላጣው አሰልጣኝ በረከት ደሙ መልካም ዜና ነው ።
በመቐለ 70 እንደርታ በኩል መድሐኔ ብርሃኔ እና ቤንጃሚን ኮቴ በቅጣት ተመስገን በጅሮንድ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ የመናፍ ዐወል መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።
ቡድኖቹ በሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ምዓም አናብስት አንድ ጊዜ ድል ስያደርጉ በ2 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱ መቐለ 6 ግቦች ስያስቆጥር አርባምንጭ 2 ግቦች አስቆጥራል።