ከድል ጋር የተራራቁት ፈረሰኞቹ እና ብርቱካናማዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ሊጉ በአህጉራዊ ውድድሮች ከመቋረጡ በፊት የሚደረግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር ነው።
በሀያ ስምንት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ ከአራት ጨዋታዎች መልስ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለማሻሻል ከአደጋው ክልል ለመራቅ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ከሚጠበቅባቸው ብርቱካናማዎቹን ይፋለማሉ።
በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ሽንፈት ገጥሟቸው ደረጃቸውን ያጡት ፈረሰኞቹ ጠንካራ ቡድኖች በገጠሙባቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች ላይ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥብ አንዱ ብቻ በማሳካት በውጤት ረገድ ደካማ ሳምንታት አሳልፈዋል፤ ሆኖም በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ነገ ድል ማድረግ ከቻሉ ዳግም ወደ ፉክክሩ የሚመለሱበት ዕድል በእጃቸው ይገኛል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድናቸው ዳግም ወደ ቀደመው የውጤት ጎዳና እንዲመለስ ለግብ ማስቆጠር ችግራቸው መላ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል፤ ቡድኑ ተከታታይ ድሎች ባስመዘገበበት ወቅት በስድስት ጨዋታዎች አስር ግቦች በማስቆጠር ለውጤቱ የአንበሳውን ድርሻ የተወጣው የማጥቃት ጥምረቱ በቅርብ ሳምንታት ከቀደመው ስልነቱ ጋር አይገኝም። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው። በነገው ወሳኝ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ለማግኘትም ለተጠቀሰው የግብ ማስቆጠር ችግር መፍትሔ ማበጀት የቡድኑ ትልቁ የቤት ስራ ነው።
ካሉበት አስጊ ቀጠና ለመውጣት ድል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በሀያ አንድ ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ይገኛሉ።
ብርቱካናማዎቹ ከመቀመጫ ከተማቸው ከወጡ በኋላ ማሸነፍ አልቻሉም፤ ድል ካደረጉም አስር የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥረዋል። ቡድኑ ዘለግ ላሉ ሳምንታት ከድል ጋር መኳረፉም ደረጃው አሽቆልቁሎ በወራጅ ቀጠናው ካሉት ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ጠቧል፤ ከስጋት ቀጠናው መጠነኛ እፎይታ የሚሰጣቸው ድል ለማግኘትም ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች አድርገው መቅረብ ግድ ይላቸዋል።በቀዳሚነትም ባለፉት አስር ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወት የግብ ዕድሎች በመፍጠርም ይሁን በአፈፃፀም ረገድ መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ድክመት ነው።
በተለይም ቡድኑ ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል በሚገባበት ጊዜ የሚያጥረውን የማጥቃት ሀሳብ ማስተካከል ይኖርበታል። ከምንም በላይ ደግሞ ሁነኛ እና አይምሬ የአጥቂ አማራጭ አለመያዙ የፊት መስመሩ አስፈሪ እንዳይሆን አድርጎታል። ከዚህ መነሻነት በነገው ጨዋታ የስልነት ችግር አደጋ ውስጥ እንዳይከተው ያሰጋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ25 ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 15ቱን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 5ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል። ፈረሰኞቹ 40፣ ብርቱካናማዎቹ 20 ጎሎች አስቆጥረዋል።