በስድስት ጎሎች ያሸበረቀው የፋሲል ከነማ እና መቻል ጨዋታ በዐፄዎቹ የ4ለ2 አሸናፊነት ተደምድሟል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት መቻል ከወልዋሎ ፣ ፋሲል ደግሞ ከባህር ዳር ጋር ያለ ጎል ከፈፀሟቸው ጨዋታዎች ጦሩ በሦስቱ ላይ ለውጥን ሲያደርግ ግሩም ሐጎስ ፣ ዮዳሄ ዳዊት እና ዮሐንስ መንግሥቱን በዳዊት ማሞ ፣ ዓለምብርሀን ይግዛው እና ምንይሉ ወንድሙ ሲተኳቸው አፄዎቹ በአንፃሩ በሁለቱ ላይ በወሰዱት ቅያሪ ቃልኪዳን ዘላለምን በብሩክ አማኑኤል ፣ ሀብታሙ ተከስተን በአሚር ሙደሲር ቦታ ለውጠው ቀርበዋል።
በትላንትናው ዕለት በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቱን ላጣው የዳጉ ስፖርት ጋዜጠኛ ኑርሁሴን ዓሊ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ቢያስመለክተንም የጠሩ ዕድሎች ግን መታየት የጀመሩት ከውሀ ዕረፍት ሲመለስ ነበር። ከተጠቀሰው ደቂቃ በኋላ ከመስመር አብዝተው መነሳትን መርጠው የታዩት መቻሎች 28ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ ከቀኝ በረከት ደስታ ያገኘውን ወደ ውስጥ ሲያሻግር የግብ ዘቡ ፋሲል እና ተከላካዩ ምኞት ኳሷን ከነካኳት በኋላ በነፃነት ያገኘው አቤል ነጋሽ መረቡ ላይ አሳርፎ ነበር ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገው።
ጎልን ካስተናገዱ በኋላ በሽግግር አጨዋወት ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ወደ ማድረጉ የገቡት አፄዎቹ 42ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አግኝተዋል። ወጣቱ የግራ መስመር ተከላካይ ኪሩቤል ዳኜ ከማዕዘን ያሻማትን ኳስ ነፃ ሆኖ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግንባር በመግጨት አስቆጥሮ ነበር ቡድኑን 1ለ1 ያደረገው።
በሁለተኛ አጋማሽ በተመለሰው ጨዋታ መቻሎች መጠነኛ የአጀማመር ብልጫን በመውሰድ በበረከት ደስታ አማካኝነት ሙከራን ማድረግ ቢችሉም በመከላከሉ የነበራቸውን ድክመት ያስተዋሉት ፋሲሎች ቀስ በቀስ ከፍ ባለ ተነሳሽነት በሽግግር በመጫወት በጎል መድመቅ ጀምረዋል። 58ኛው ደቂቃ ማርቲን ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻማ አስቻለው ታመነ በግንባር ገጭቶ በአግባቡ ያላራቃትን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በደረቱ አቀዝቅዞ ድንቅ ግብን በማስቆጠር ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል።
የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት አፄዎቹ ጌታነህ ካደረጋት ሙከራ መልስ በ69ኛው ደቂቃ ቢኒያም ጌታቸው በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ወደ ሳጥን እየነዳ ገብቶ አሊዮንዚ መረብ ላይ ሦስተኛዋን ጎል አክሏል ፣ ግቧ ስትቆጠር የመቻል አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጪ ነበረች በሚል ቅሬታቸውን በዕለቱ ዳኞች ላይ አሰምተዋል።
ጨዋታው ቀጥሎ 76ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ዳኜ ከማዕዘን አሻምቶ ምኞት ደበበ በግንባር በመግጨት አራተኛዋን ጎል ከመረብ ካሳረፈ በኋላ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች መጠነኛ መቀዛቀዞችን ያሳዩት ፋሲሎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተጫዋች ቅያሪን ባደረጉት መቻሎች መጠነኛ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። ተቀይሮ የገባው ፊሊሞን ገብረፃዲቅ ቋሚ ብረት ከመለሰበት ከሰከንዶች መልስ 90+7 ከአብዱ ሙታሎቫ እዛው ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ መቻልን ከሽንፈት ማዳን ያልቻለች ግብ አድርጎ ጨዋታውም በፋሲል ከነማ የ4ለ2 አሸናፊነት ተቋጭቷል።