ሪፖርት | ፈረሰኞቹን ከብርቱካናማዎቹ ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

ሪፖርት | ፈረሰኞቹን ከብርቱካናማዎቹ ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በሳምንቱ መዝጊያ መርሐግብር የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ 0-0 ተለያይተዋል።

በኢዮብ ሰንደቁ

ባሳላፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ 1-0 ሽንፈትን ያስተናገዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ቶሎሣ ንጉሤ ፣ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ ፣ አማኑኤል ኤርቦን በማሳረፍ በምትኩ ፍሪምፖንግ ክዋሜ ፣ ፍፁም ጥላሁን እና ሀብታሙ ጉልላትን ሲያስገቡ በተቃራኒው ድሬዳዋ ከተማዎች ቴዎድሮስ ሀሙን በኢስማኤል አብዱልጋኒዩ ፣ አቤል አሰበን በጀሚል ያዕቆብ እና ሙኸዲን ሙሳን በመስዑድ መሐመድ በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ሁለቱንም ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው የምሽቱ መርሐግብር ለሁለቱም ቡድኖች ወደ ድል ለመመለስ እጅግ አስፈላጊ ጨዋታ ነበር። ጨዋታው ጥሩ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች የማጥቃት ዒላማቸውን ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ለማድረግ ሲሞክሩ በተቃራኒው ድሬዳዋ ከተማዎች የሜዳው መሐል ላይ ብልጫ በመውሰድ የጎል እድሎችን ለማግኘት ሲጥሩ ተስተውሏል።

22ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን ተካላካዮች ታግሎ በማለፍ ከሳጥኑ ቀኝ ላይ በመሆን የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሐንስ መልሶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ጫና በመፍጠር አጥቅተው መጫወት የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 45+3′ ላይ ከቀኝ መስመር መነሻውን ያደረገውን የቅጣት ምት ፍፁም ጥላሁን በጥሩ ሁኔታ በግንባሩ ቢገጨውም ግብ ጠባቂው አላዛር ማረነ ወደ ውጭ አውጥቶታል። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ በብዙ መመዘኛ ተሻሽለው የቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመቅረብ የቅዱስ ጊዮርጊስን ተከላካዮች ሲፈትኗቸው ተስተውሏል። ቅዱስ ጊዮርጊሶችም መነሻቸውን ከራሳቸው ግብ ክልል ያደረጉ ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በመቀጠም ለማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም ዓይነት ዒላማውን የጠበቀ የጎል ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ያለ ግብ 0-0 ተጠናቋል።