ከዚህ ቀደም ባጋራናቹሁ መረጃ መሰረት ከሰሞኑ ወደ አዲስ ክለብ ለማምራት በድርድር ላይ የቆየው ዮሴፍ ታረቀኝ ጉዳይ መቋጫውን አግኝቷል።
በዚህ ዓመት መጀመርያ ላይ ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሎ ለሳምንታት ቡድኑን ያገለገለው ዮሴፍ ታረቀኝ ከክለቡ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ለወራት ቡድኑን ሳያገለግል መቆየቱ ይታወሳል።
በዚህ መነሻነት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በመለያየት ወደ ሌላኛው የሊጉ ተሳታፊ ክለብ መቻል ለማምራት ከጫፍ መድረሱን በወቅቱ መዘገባችን ይታወቃል።
ሆኖም የዝውውር ሂደቱ መጠነኛ እክሎች በማስተናገዱ ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ቢወስድም በመጨረሻም ከሰሞኑ የመስመር አጥቂው ለማስፈረም የተደረገው ጥረት ተሳክቶላቸው መቻሎች ዮሴፍ ታረቀኝን ለሁለት ዓመት ስለማስፈረማቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።
ዮሴፍ የእግርኳስ ህይወቱን በአዳማ ከተማ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ የዘለቀ ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን ዘንድሮ ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት ለወራት መጫወቱ ይታወሳል። የመስመር አጥቂው በ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ወጣት ተጫዋች በመባል የተመረጠ መሆኑ ይታወቃል።