ነጻነት ገብረመድኅን ከስሑል ሽረ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሆኗል።
ባለፈው ክረምት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ለቆ ስሑል ሽረን በመቀላቀል ላለፉት ስድስት ወራት በክለቡ ቆይታ የነበረው ተከላካዩ ነጻነት ገብረመድኅን ከቡድኑ ጋር በጋራ ስምምነት ተለያይቷል። ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ እናት ክለቡ ስሑል ሽረን ካገለገለ በኋላ በ2013 ከክለቡ ጋር ተለያይቶ በወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቆይታ የነበረው ተጫዋቹ አንጋፋው ክለብ ወደ ሊጉ እንዲመለስ አስተዋጾ ካደረገበት እና በከፍተኛ ሊጉ ምርጥ ቡድን ከተካተተበት የውድድር ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ስሑል ሽረ ተመልሶ ላለፉት ወራት ቆይታ ቢያደርግም ቀሪ ውል እያለው ከቡድኑ ጋር በስምምነት መለያየቱ እርግጥ ሆኗል።
ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ ስሑል ሽረ ተመልሶ ቡድኑን በአምበልነት የመራው ነጻነት በውድድር ዓመቱ በአስራ አምስት ጨዋታዎች ተሰልፎ መጫወቱ ይታወሳል። ከዚህ ቀደም ከዮሴፍ ኃይሉ፣ አዲስ ግርማ እና ፋሲል ገብረሚካኤል ጋር ተለያይተው ዊልያም ሰለሞንን ያገዱት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ ከአምበሉ ጋር መለያየታቸውን ተከትሎ ቡድኑን የለቀቁ ተጫዋቾች ቁጥር አራት ደርሷል።