በቅርቡ ‘በሴሪ ኤ’ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ትውልደ ኢትዮጵያዊ አዲስ ክለብ ተቀላቅሏል
በ2015 የቶሪኖ ታዳጊዎች ቡድን ተቀላቅሎ ላለፉት ዓመታት በአራት የቱሪኑ ክለብ ታዳጊ ቡድኖች ቆይታ ካደረገ በኋለ በቅርቡ ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሮን ሲማግሊቼላ በውሰት ውል ‘የሴሪ ሲ’ ክለብ የሆነው ቴርናናን ተቀላቅሏል።
ከወራት በፊት ቶሪኖ አታላንታን ሁለት ለአንድ ባሸነፈበት የሴሪ ኤ ጨዋታ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ለተጨማሪ ልምድ ‘በሴሪ ሲ’ ምድብ ሁለት ላይ እየተሳፈ የሚገኘው እና በሁለተኛ ደረጃነት ለተቀመጠው ክለብ በስድስት ወራት የውሰት ውል ተቀላቅሏል።
የቱሪን ተወላጅ ከሆነች እናቱ ካቲያና በዝዋይ ተወልዶ በሚላን ከተማ በማደጎነት ካደገው የቀድሞ ተጫዋች ኢትዮጵያዊው አባቱ ማቲያ ሲማግሊቼላ በቱሪን ከተማ የተወለደው ይህ ከወዲሁ ትልቅ ትኩረት የሳበው ወጣት በ2022 በእንግሊዙ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን በ2005 ከተወለዱት ምርጥ ተጫዋቾች መካከል መካተቱ ሲታወስ ባለፈው ዓመት ደግሞ በ ‘Pallone Granata award’ በምርጥ ወጣት ተጫዋችነት ዘርፍ ተሸለሚ ነበር።
ተስፈኛው ተጫዋች በጣልያን ወጣት ብሔራዊ ቡድን ስር በአውሮፓ ዋንጫው ባሳየው ብቃት በክረምቱ የዝውውር መስኮት የፈረንሳዩን ፒ ኤስ ጂ ጨምሮ የበርካታ የአውሮፓ ክለቦች ትኩረት መሳብ ቢችልም በእናት ክለቡ ለመቆየት መወሰኑ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ለተጨማሪ ልምድ ወደ ‘ሴሪ ሲ’ ክለብ አምርቶ በጨዋታዎች መሳተፍ ጀምሯል።
ከዚህ ቀደም ስለተጫዋቹ የእግር ኳስ ሕይወት ያዘጋጀነውን ፅሑፍ ከታች ባለው link ያገኙታል