የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ስብስቧን አሳውቃለች

የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ስብስቧን አሳውቃለች

የኢትዮጵያ ቀጣይ ተጋጣሚ የሆነችው ግብፅ ሞ ሳላን ጨምሮ ወሳኝ ተጫዋቾች የጠራችበትን የ24 ተጫዋቾች ስብስብ ይፋ አድርጋለች።

ለ2026 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረጉ የምድብ የማጣሪያ ፍልሚያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት 12 ካዛብላንካ (ሞሮኮ) በሚገኘው ዛውሊ ስታዲየም ከግብጽ ጋር እንዲሁም መጋቢት 15 ኤል ጀዲዳ (ሞሮኮ) በሚገኘው ኤል አብዲ ስታዲየም ከጂቡቲ ጋር ወሳኝ ጨዋታዎች ይጠብቀዋል። ለሁለቱ ጨዋታዎች አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ዝግጅታቸውን ካሳለፍነው ሀሙስ ጀምሮ እያከናወኑ ይገኛሉ።

የዋልያዎቹ የመጀመሪያ ተጋጣሚ የሆነችው ግብፅ በአሠልጣኝ ሆሳም ሀሰን እየተመራች ከኢትዮጵያ እና ከሴራሊዮን ጋር ላለባት ጨዋታዎች በትናትናው ዕለት ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርባለች። በዚህም አራት የግብ ዘብ፣ ሰባት ተከላካዮች፣ ዘጠኝ አማካዮች እንዲሁም አራት አጥቂዎች በስብስቡ ተካተዋል።

በምርጫው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው የሊቨርፑሉ ኮከብ መሐመድ ሳላ፣ የማንቸስተር ሲቲው ዑማር ማርሙሽ እና መሐመድ ትሬዜጊትን ጨምሮ 6 ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ተመርጠዋል። ከሀገር ውስጥ ሊግ ደግሞ አል አህሊ 6 ተጫዋቾችን ሲያስመርጥ ዛማሌክ በበኩሉ 5 ተጫዋቾችን አስመርጧል።

ከምርጫው ጋር በተያያዘ ብዙዎችን ያስገረመው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው የዛማሌኩ የግብ አዳኝ ናስር ማንሲ እና የፕሪምየር ሊጉ እንዲሁም የቻምፒየንስ ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው የአል አህሊው አማካኝ ኢማም አሾር በስብስቡ አለመካተታቸው እንደሆነ እየተሰማ ይገኛል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ዛሬ (አንዳንዶቹ ነገ) ካይሮ ላይ የሚሰባሰቡ ሲሆን በነገው ዕለት ወደ ሞሮኮ እንደሚያቀኑና ከኢትዮጵያው ጨዋታ በፊት ሁለት ወይም ሦስት ልምምዶችን ብቻ አከናውነው ፍልሚያውን እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

የ7 ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤቷ ግብፅ በአራት የምድቡ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነጥብ በመጋራይ ምድቡን በ10 ነጥብ እየመራች ትገኛለች።