መቐለ 70 እንደርታ አማካዩን ሲያስፈርም የተጣለበት እገዳም ተነስቷል።
በዝውውር መስኮቱ ተሳትፎ ሳያደርጉ የቆዩት መቐለ 70 እንደርታዎች ላለፈው አንድ ዓመት በሲዳማ ቡና ቆይታ የነበረው ጋናዊው የተከላካይ አማካይ ኢማኑኤል ሳባን ላርዬ የግላቸው አድርገዋል።
በ2010 አሳዳጊ ክለቡ ኸርትስ ኦፍ ኦክ በመልቀቅ ድሬዳዋ ከተማን ተቀላቅሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የተዋወቀው ተጫዋቹ ከብርቱካናማዎቹ ጋር የነበረው ውል ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ጃፓን አቅንቶ
በኦኮሺያስ ኪዮቶን ቆይታ ካደረገ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለመቻል፣ አርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ሲዳማ ቡና መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር የነበረው የአንድ ዓመት ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ማረፍያው መቐለ 70 እንደርታ አድርጓል።
የ29 ዓመቱ ተጫዋች በውድድር ዓመቱ በአስራ አምስት ጨዋታዎች ተሰልፎ 1260 ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለ ሲሆን ወደ ምዓም አናብስት የሚደረገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ ከቀናት በፊት የህክምና ምርመራውን ካጠናቀቀ በኋላ ከደቂቃዎች በፊት ፌርማውን አኑሯል ፤ ታታሪው የተከላካይ አማካይ በ2015 በተካሄዱ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ሀገሩ ጋናን መወከሉም ይታወሳል።
ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ክለቡ የቀድሞ ተጫዋቹ ቢያድግልኝ ኤልያስን ውዝፍ ደሞዝ መክፈሉ ታውቋል፤ በተጫዋቹ ጉዳይ ዝውውሮች እንዳይፈፅም ዕግድ ላይ የነበረው ክለቡ ክፍያውን ማጠናቀቁ ተከትሎ ዕገዳው እንደተነሳለት ለማወቅ ችለናል።