መቐለ 70 እንደርታ ግብ ጠባቂ አስፈረመ

መቐለ 70 እንደርታ ግብ ጠባቂ አስፈረመ

መድንን ለመቀላቀል ተስማምቶ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሠራ የሰነበተው ግብ ጠባቂ ምዓም አናብስትን መቀላቀሉ እርግጥ ሆኗል።

ከሦስት ዓመት የስድስት ወር የሲዳማ ቡና ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ኢትዮጵያ መድንን ለመቀላቀል ከስምምነት በመድረስ የሕክምና ምርመራ አጠናቆ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ጀምሮ የነበረው ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በሊጉ መሪ የቀናት ቆይታ ካደረገ በኋላ ዝውውሩ በአንዳንድ ጉዳዮች ባለመሳካቱ በአንድ ዓመት ውል ለመቐለ 70 እንደርታን ፌርማውን አኑሯል።

ከዚህ ቀደም በወላይታ ድቻ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ሀምበርቾ እና ደቡብ ፖሊስ ከ2014 ጀምሮ ደግሞ በሲዳማ ቡና ሲጫወት የቆየው ግብ ጠባቂው በዝውውር መስኮቱ መቐለ 70 እንደርታን የተቀላቀለ ሁለተኛው ተጫዋች ሲሆን ለቋሚነትም ከሶፎንያስ ሰይፈ ጋር የሚፎካከር ይሆናል።

ባለፈው የውድድር ዓመት ባሳየው ጥሩ ብቃት በሚያዚያ ወር ወደ የተባበሩት ዓረብ ኤመራቱ ክለብ ሸባብ አል ሂላል ለመቀላቀል በግሉ ከተስማማ በኋላ ሲዳማ ቡናዎች ተጫዋቹን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ዝውውሩ መክሸፉ የሚታወስ ሲሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ወደ ሌላው የሊጉ ክለብ ማምራቱ ተረጋግጧል።