መቐለ 70 እንደርታ የዝውውር መስኮቱ ሦስተኛ ፈራሚ ለማግኘት ተቃርቧል

መቐለ 70 እንደርታ የዝውውር መስኮቱ ሦስተኛ ፈራሚ ለማግኘት ተቃርቧል

ካሜሮናዊው አጥቂ ምዓም አናብስቱን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

ቀደም ብለው በሲዳማ ቡና ቆይታ የነበራቸው ጋናዊው አማካይ ኢማኑኤል ላርያ እና ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ የግላቸው ያደረጉት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ካሜሮናዊው አጥቂ ዳንግሞ ማን ይክረ ለማስፈርም ከጫፍ ደርሰዋል።

ላለፈው አንድ ዓመት በቱርክ ብቻ እውቅና በተሰጣት ራስ ገዝ ሀገር በሆነችው ሰሜን ሳይፕረስ በሚገኘው ‘ Yenicami AK’ ሲጫወት የቆየው ይህ የሀያ ሰባት ዓመት አጥቂ ከብሬሴሪስ እግር ኳስ አካዳሚ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በሀገሩ ክለብ ኮሎምፔ ስፖርት፣ በግብፁ ምስር አል ማቃሳ እና በሩዋንዳው ኪጋሊ መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ለመቀላቀል ተስማምቶ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ይገባል።

በ2020 በአፍሪካ ሀገራት ሻምፕዮና (ቻን) እስከ ግማሽ ፍፃሜ በተጓዘው የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን አባል የነበረው ንግኖዋ ሀፕሞ ማን ይክረ ዳንግሞ  ለሀገሩ አምስት ጨዋታዎች ማድረግም የቻለ ሲሆን ተጫዋቹን ለማስፈረም በሂደት እንዳለ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ይፋ ያደረገው ክለቡ በቀጣይ ቀናት ዝውውሩን ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።