የተከላካዩ አሁናዊ ሁኔታ

የተከላካዩ አሁናዊ ሁኔታ

የነጻነት ገብረመድኅን ጉዳይ መቋጫ ለማግኘት ተቃርቧል።

በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የዝውውር መስኮት አነጋጋሪ ከነበሩ የዝውውር ሂደቶች አንዱ የሆነው የተከላካዩ ነጻነት ገብረመድኅን ጉዳይ መቋጫ ሊያገኝ ተቃርቧል። ቀድም ብሎ ላለፉት ስድስት ወራት ከተጫወተበት ስሑል ሽረ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት አፍርሶ ወደ ሌላው የሊጉ ክለብ ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ የነበረው ተጫዋቹ ከስሑል ሽረ አመራሮች ጋር ካደረገው ውይይት በኋላ ዳግም ክለቡን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሶ ልምምድ ጀምሯል። ቡድኑን በአምበልነት ባገለገለበት የመጀመሪያ ዙር ቆይታው አስራ አምስት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 1350′ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆየው ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር የነበረውን ውል ካፈረሰ በኋላ ሌላው የሊጉ ክለብ ለመቀላቀል ተስምማቶ የሕክምና ምርመራ ማጠናቀቅ ቢችልም ዝውውሩ ከመገባደዱ በፊት ከስሑል ሽረ የበላይ አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት ዳግም ወደ ክለቡ ለመመለስ ተስማምቶ በሽረ እንዳሥላሴ ከተማ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ጀምሯል።

ከስሑል ሽረ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ባልተከፈለ ደሞዝ ምክንያት እግድ ላይ ያለው ክለቡ የጋናዊው አጥቂ ቢስማርክ አፖንግን ውዝፍ ደሞዝ ለመክፈል በሂደት ላይ እንዳለ እና በቀጣይ ቀናት ሂደቱን እንደሚያጠናቅቅ ለማወቅ ተችሏል።