ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ግብ ጠባቂ በ31 ዓመቱ ጓንቱን ሰቅሏል።
በ2010 የደቡብ አፍሪካውን ኦርላንዶ ፓይሬትስ ለቆ ወደ መቐለ 70 እንደርታ በማምራት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር የተዋወቀው እና በኢትዮጵያ ቆይታው ለመቐለ 70 እንደርታ እና ሲዳማ ቡና መጫወት የቻለው ኢኳቶሪያል ጊንያዊው ፊሊፕ ኦቮኖ ከአስራ ስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ጓንቱን በመስቀል ወደ አሰልጣኝነት ሞያ ገብቷል።
በሞንጎሞ ከተማ የተወለደው እና በማርያ ኦክሲሊያዶራ የተባለ ክለብ እግር ኳስን የጀመረው ግብ ጠባቂው በቆይታው ሶኒይ ኤላ ንጉማ፣ ዲፖርቲቮ ሞንጎሞ፣ ኦርላንዶ ፓይሬትስ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ፉትሮ ኪንግስ እና በሲዳማ ቡና መጫወት የቻለ ሲሆን ለሀገሩ የኢኳቶሪያል ጊኒ ብሔራዊ ቡድንም በአርባ አራት ጨዋታዎች አገልግሏል።
ገና በአስራ ስድስት ዓመቱ ለዋናው ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የጀመረው ግብ ጠባቂው ሀገሩን በሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች የወከለ ሲሆን ቡድኑን በአምበልነት እስከመምራትም ደርሷል። መቐለ 70 እንደርታ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ ድርሻ የተወጣው እና በክለቡ ደጋፊዎች ተወዳጅ የነበረው ኦቮኖ በ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ መሸለሙ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ከተጫዋችነት ራሱን በማግለል በኢኳቶርያል ጊኒ ዋናው ሊግ ተሳታፊ የሆነውን ሪል ቴካ ማሰልጠን ጀምሯል።