የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነው ጅማ አባ ጅፋር በሀገሪቱ ሦስተኛ ዕርከን ከሆነው ሊግ አንድ ውድድር መውረዱ እርግጥ ሆኗል።
በ2009 ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት ጅማ አባ ጅፋሮች በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያቸው በነበረው የ2010 የውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ በማንሳት የማይረሳ ታሪክን መፃፍ ችለዋል። ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግም እንዲሁ የተሳትፎ ታሪክ የነበረው ክለብ እንደሆነ አይዘነጋም።
ታዲያ ከዚህ ስኬት ማግስት ጀምሮ ከፋይናንስ አስተዳደር ጋር የተያያዙ የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሙት የዘለቀው ጅማ አባ ጅፋር በ2014 የውድደር ዘመን ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱም አይዘነጋም። በቀጣይ ቡድኑ ዳግም ወደ ሊጉ ለመመለስ ከተሰሩ ስህተቶች ትምህርት በመውሰድ በቁጭት ስራዎችን በመስራት የተሻለ ነገር ይኖራል ተብሎ ሲጠበቅ ክለቡ በቁልቁለት ጉዞዎ ቀጥሎበት በ2016 ደግሞ ወደ ሊግ አንድ መውረዱ ይታወቃል።
በ2017 የውድድር ዘመን በምድብ ሀ የተደለደለው ጅማ አባ ጅፋር ከተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ አስቸጋሪውን ውድድሩን ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታውን ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር አድርጎ 2-1 መሸነፉን ተከትሎ በምድቡ ከሚወርዱ አራት ክለቦች መካከል አንዱ መሆኑ ተረጋግጧል።
ይህን ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋር ዳግም ወደ ሀገሪቱ ውድድር ለመመለስ ባለበት ክልል በሚካሄደው የክልል ውድድር ተሳታፊ በመሆን በሚያስመዘግበው ውጤት መሠረት ለክልል ክለቦች ሻምፒዮን ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል።
በቀጣይ የክለቡ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ለማወቅ የክለቡን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።