የግል አስተያየት | ለትችቶች በሩን የከረቸመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

የግል አስተያየት | ለትችቶች በሩን የከረቸመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ፤ እውነታውን በመሸሽ እግር ኳሳችንን መለወጥ ይቻላልን?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከነ ፈርጀ ብዙ ችግሮቹ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ እየተራመደ በዘመን ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሷል ፤ በዚህ ሂደት ለዘመናት በችግርነት የሚነሱት የታዳጊዎች ስልጠና ጉዳይ ፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ፣ የስልጠና መንገድ ወዘተ አሁንም ድረስ በችግርነት መቅረባቸውን ሲቀጥሉ ሌላው ብዙም ልብ ያልተባለው እና እግር ኳሳችንን እግር ከወርች የጠፈረው ጉዳይ እግር ኳሳችንን በተመለከተ የሚሰጡ አስተያየቶችን በተለይም አሉታዊ ይዘት ያላቸውን በጥርጣሬ የመመልከት አለፍ ሲል ሀሳብ ሰጪዎችን በአሉታዊ ግብረመልሶች ለማሸማቀቅ የሚደረገው ጥረት እግር ኳሳችንን የተጠናወተው ክፉ ደዌ ሆኗል።

እግር ኳስ ዓለምአቀፋዊ ስለመሆኑ የጋራ መግባባት ቢኖርም የኢትዮጵያ እግር ኳስን ግን በተወሰነ መልኩ በአንዳንድ መዳኛዎች በተለየ መነፅር መመልከት ተገቢ ይመስላል ፤ በተለይም ፍፁም በፈተና በተሞላ መንገድ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው ከብዙዎች መካከል በእሳት ተፈትነው ተጫዋች ሆነ አሰልጣኝ የመሆኑን “ልዩ” ዕድል ያገኙትን ግለሰቦች በልዩነት መመልከት እና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ይታመናል ፤ ነገርግን ይህን ሀሳብ ያለልክ በማጦዝ ተጫዋቾች ሆነ አሰልጣኞች በፍፁም ሊነኩ(ሊተቹ) አይገባም ማለት ግን እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባ ዓብይ ጉዳይ ነው። ተፈትነው እዚህ የደረሱትን እነዚህ አካላትን በስስት ብንመለከታቸውም ሲያለሙ ማወደስ ሲሳቱ ደግሞ ገንቢ ትችት ማቅረብ ያለ እና የሚኖር ሃቅ ነው።

እግር ኳስን የተለየ ከሚያርጉት ባህሪያቱ አንዱ ካለው ሰፊ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት አንፃር ሁሉም ሰው ሀሳብ እንዲሰጥበት ክፍት የመሆኑ ጉዳይ አንዱ ነው ፤ እግር ኳስን በሰፈር ደረጃ በልጅነቱ በጥቂቱ ከሞከረው ግለሰብ አንስቶ በእግር ኳሱ በሙያተኝነት አልፈው በሚሰጧቸው በሳል ሀሳቦች የመገናኛ ብዙሃንን ትርክት መቆጣጠር እስከሚችሉ የእግር ኳስ ተንታኞች ድረስ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሁሉም ሰዎች ሀሳብ የተጋለጠ እንደሆነ ይታወቃል።

ታድያ በዚህ ሂደት የትኛውም ግለሰብ በመረዳቱ ልክ ስለሚወደው እግር ኳስ ሀሳቦችን ሲሰጥ ይደመጣል ይሄ ደግሞ ያለ እና የሚኖር ሃቅ ነው ፤ የሀሳቡ ትክክለኝነት ቀዳሚ ጉዳይ ባይሆንም ሀሳቦች ፤ በሀሳቦቹ ላይ የተመሰረቱ አስተያየቶች የሚጠበቁ ነገሮች ሆነው ሳለ በእኛ እግር ኳስ ከዚህ ሃቅ በተፋታ መልኩ የሚመራ ይመስላል።እግር ኳሳችን አስተያየቶችን የሚረዳበት መንገድ በአውንታዊ አውድ እንጂ አሉታዊ አስተያየቶችን ለማስተናገድ የተሰራን አንመስልም።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በዚህ ረገድ የራሱ ያልተፃፈ መተዳደርያ ያለው ይመስላል ፤ “አወድሱን እንጂ ስለምን ትተቹናላችሁ” የሚለው አመክንዮ የለሽ ብሂል የእግር ኳሳችን ገዢ ትርክት ከሆነ ሰነባብቷል ፤ በዚህ እሳቤ በውዳሴው ጊዜ አንገታቸውን ቀና አድርገው አለን አለን የሚሉ በትችቶች ወቅት ደግሞ “አትናገሩኝ !” ባዩ ብዙ ነው።

ሀሳቦች መሰጠታቸው ያለ እና የሚኖር ከሆነ ሙገሳም ትችትም የሚኖሩ ነገሮች መሆናቸው እሙን ነው ፤ ታድያ ሲንቆለጳጰሱ ለመታበይ የቀረቡት የእግር ኳሱ ተዋንያን (ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች ፣ አመራሮች) ትችቱ ሲመጣ ደግሞ ሰይፋቸውን ለመምዘዝ ሲሯሯጡ ማየት በእራሱ ጥያቄ የሚፈጥር ነው ፤ ጉዳዩን በሚዛናዊነት ለተመለከተው ሰው በየትኛውም የሙያ መስክ ጥሩ ሲሰራ ማሞገስ ስህተቶች ሲኖሩ ደግሞ ትችቶች መሰንዘር ይጠበቃል።

ታድያ ሁለቱን ስሜቶች በሚዛን ለማስተናገድ የሚቸገሩት የሀገራችን የእግር ኳስ ተዋናዮች በፈርጀ ብዙ ችግሮች ተይዞ ለብዙሃኑ የብሔራዊ ደስታ ምንጭ ለመሆን ሲቸገር በሚስተዋለው እግር ኳሳችን የሚሰጡ አስተያየቶች ከሙገሳዎች ይልቅ ለትችቶች የቀረቡ ስለመሆናቸው የሚያሻማ አይደለም።

ይህን ተከትሎ ውዝግቦች እና እሰጣ ገባዎች መመልከት የእግር ኳሳችን የሰርክ ተግባር ሆኗል ታድያ በዚህ ሂደት ውስጥ ቀዳሚው መዛነፍ የሚመነጨው ሀሳቦችን(አስተያየቶችን) ካለማክበር የሚመነጭ ነው ፤ የትኛውም ሀሳብ የሰጠው አካል ማን ይሁን ማን ትክክል ሆነ አልሆነ ሀሳቡ (አስተያየቱ) በራሱ መከበር ይገባዋል።

ለአብነትም የስፖርቱ መገናኛ ብዙሃን የጨዋታ ውጤትን ከመዘገብ ባለፈ ጠለቅ ያለ ትንተናዎችን ፣ አስተያየቶችን ማቅረብ በመሰረታዊነት ከተቋቋሙበት አላማዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ ባለሙያዎች የግል ምልከታቸውን በነፃነት የሚሰጡበት ምህዳር በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየጠበበ አሁን ላይ ሃሳቦችን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙርያ መስጠት ክፉኛ የሚያስኮንን የተወገዘ ተግባር ተደርጎ እንዲወሰድ ተደርጓል።

የትኛውም ግለሰብ የራሱ የሆነ ሀሳብ አለው ፤ ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብትም እንዲሁ ከሀሳቡ ባሻገር መስማማት አለመስማማት ደግሞ ሀሳቡን ለሚመዝነው ሰው የተተወ ነው። በመሆኑም የትኛውም የሚድያ ባለሙያ ሆነ ሌላ አካል ሀሳቡን ሆን ብሎ ሌሎችን በሚያስከፋ እና ተገቢ ባልሆነ መንገድ እስካልገለፀ ድረስ ሀሳቡን መሞጎት እንጂ ሌላ ርቀት መጓዝ ባልተገባ ነበር።

ለወትሮው የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት በተነፈገው የሀገር ቤት እግር ኳስ ላይ ይህንን አስተሳሰብ ሰብረው በተወሰነ መልኩ ሀሳቦችን ለማንሸራሸር የሚጥሩትን ደግሞ በተለያዩ መንገድ ለማሸማቀቅ እና ሀሳብን መግለፅን ለማነወር የሚደረጉ ጥረቶች የአደባባይ ሀቆች ናቸው ፤ እግር ኳሳችን እንደ እውነቱ ከሆነ የሚገኝበት ደረጃ ክፉኛ ስለመሆኑ አስታዋሽ የሚሻ አይደለም። በመሆኑን ስለእግር ኳሳችን ደካማነት ያነሱ በዚህ ሂደት ደካማ አፈፃፀም አላቸው ያላቸው አካላት ላይ አስተያየት መስጠታቸው ነውር የሚሆንበት አግባብ የለም በመሆኑም መራራውን ሃቅ ተጋፍጦ ራስን ለማሻሻል አለፍ ሲልም እግር ኳሱን ለመቀየር መታተር እንጂ “አትናገሩን !” ማለቱ አይበጅም።

ሌላኛው መዛነፍ ደግሞ ለሚሰጡ አስተያየቶች ሁሉ ጆሮ መስጠትን ይመለከታል ፤ ተጫዋች ፣ አሰልጣኝ ፣ የቡድን አመራሮች ፣ ደጋፊዎች ሁሉም እንደየድርሻው በራሱ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በይበልጥ ሌሎች ስለእነሱ ያላቸው ምልከታ የሚያስጨንቃቸው ይመስላል።

በራሱ የሚተማመን የትኛውም አካል በሙገሳዎች ልቡ አይሞቅም በትችቶችም ደግሞ አይሰበርም ይህን ስንል ለሚሰጡ ሀሳቦች ሁሉ “ጆሮ ዳባ ልበስ” በሚለው የሀገሬው ብሂል ተገቢ ነው ከሚል መነሻ ሳይሆን ወደ ጆሮ የሚደርሱ አስተያየቶችን እንደ ወረዱ ተቀብሎ ወደ ውስጥ ከማስገባት ይልቅ ልየታ በመከወን የሚበጁትን ማለትም ውዳሴዎችን ብቻ ሳይሆኑ ወደ ውስጥ ቢያስገቧቸው አሁን ካሉበት ደረጃ ሊያሳድጉ ሊያሻሽሉ የሚችሉትን በመለየት ማስገባት ሌሎች ደግሞ ምክንያታዊ ያልሆኑትን ደግሞ ቦታ አለመስጠት ተገቢው መንገድ ይመስላል።

ሁሉም አካል በላቀ የሙያተኝነት ስሜት ራሱን እና ራሱን በማሻሻል ላይ ትኩረት ቢያደርግ እና ከሌሎች ምልከታ ይልቅ ለራስ ትክክለኛ ድክመትንም ጥንካሬን ያገናዘበ ምስል መያዝ ለመሻሻል ይበጃልና ይህ ጉዳይ ትኩረትን ይሻል።

ነገርግን በእግር ኳሳችን ውስጥ ያሉ ተዋንያን የቀረቡትን አስተያየቶችን መርምሮ ጠቃሚውን ከመውሰድ አልያም ሌላው ከመጣል ይልቅ ውዳሴዎቹ በሙሉ የመውሰድ አሉታዊ የሆኑትን ግን ያለአመክንዮ በታላቅ የጦረኝነት ስሜት ሲያስተናግዷቸው እና ምላሽ ለመስጠት ርቀው ሲሄዱ እንመለከታለን ይሄም መታረም የሚገባው ይመስላል።

ሌላኛው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው መዛነፍ ምንጩ ደግሞ እኛ ለውዳሴ የታጨን ነን የሚለው በእግር ኳሳችን እየገነገነ ያለ አደገኛ እሳቤ ነው ፤ ይሄም ውዳሴው በልካችን የተሰፋ ትችቱ ደግሞ በፍፁም እኛን የማይመጥን ነው የሚል ያልተፃፈ ነገርግን ብዙዎች ላይ የሚነበብ ፍፁም አደገኛ አመለካከት ነው።

ሰው ፍፁም አይደለም ብለን ከተግባባን ስህተቶች ይኖራሉ ማለት ነው ስለዚህ ስህተቶች እንዲታረሙ ደግሞ ትችቶች አስፈላጊ ናቸው ፤ በእኛ ሀገር አውድ ግን አስተያየቶቹ በይዘት ደረጃ ከሙገሳ በመጠኑ ካፈነገጡ አስተያት ሰጪውን እንደ ጠላት የመፈረጅና አስተያየት የሰጠበትን አካል ለማጥፋት በህቡዕ ተልዕኮ የተቀበለ አካል አድርጎ የማሳቀል ሙከራዎች ሲደረጉ እናያለን ይህም ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።

እንደ አብዛኞቻችን ፍላጎት እና መሻት ቢሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሁሉም በላቀ ነበር ነገርግን መሻታችን በስራ የታጀበ ባለመሆኑ አሁንም እግር ኳሳችን እየተንገራገጨ ይገኛል ፤ ለእግር ኳሳችን ከምንመኘው እድገት እና በአሁናዊ የእግር ኳሷችን ደረጃ መካከል ያለውን በግልፅ የሚታወቅ ልዩነት ለማጥፋት መጠነ ሰፊ ስራ ይጠይቃል ፤ ታድያ ይህ ጉዞ በግለሰቦች የተናጥል ጥረት ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ ስለሆነ ከመገፋፋት እና በጥርጣሬ ከተመተያየት ወጥተን ልዮነቶቻችን እያጠበብን በተመባበር ስሜት ለጋራ አላማ መስራት ይኖርብናል ፤ ለመለወጥ ደግሞ ችግሮቹን ለማድመጥ እና ለመወያየት አለፍ ሲልም የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እግር ኳሳችን ለሀሳብ ብዙሃነት ፣ ለትችቶች በሩን ወገግ አድርጎ መክፈት ይኖርበታል ነገርግን ይህ ባልሆነበት በትናናንሽ ስኬቶቻችን እየተወዳደስን መራራውን እውነት ሸሽተን እግር ኳሳችን እንዲለወጥ መጠበቅ እስከአሁን የመጣንበትን አዙሪት መድገም መሆኑ ግልፅ ነው።

በመጨረሻም የብዙሃኑ የትኩረት ማዕከል በሆነው እግር ኳስ ውስጥ ያሉ ተዋንያን በሁለቱ ፅንፍ ላሉ አስተያየቶች መጋለጣቸው የሚጠበቅ ሁነት እንደመሆኑ ሙገሳውንም ነቀፋውን በልክ በመውሰድ “ከእኛ እና እነሱ” ከሚለው አደገኛ የአጥቂ እና ተጠቂ እሳቤ ወጥተን ሁላችንም በጋራ እግር ኳሳችንን ወደምናልመው ከፍታ ለመመለስ መትጋት ይኖርብናል።