በ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚቀላቀሉ ሁለት ቡድኖች መካከል አንዱ ዛሬ ይታወቅ ይሆን ?
የሀገሪቱ ሁለተኛ የሊግ ዕርከን ውድድር የሆነው እና ፕሪምየር ሊጉ የሚቀላቀሉ ቡድኖች የሚለዮበት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዘንድሮም በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል። ውድድሩ ሊጠናቀቅ የጥቂት ሳምንታት ዕድሜ በቀረው በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ያለው የምድብ “ሀ” ውድድር ዛሬ በሚካሄድ አንድ ጨዋታ ለከርሞ ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀል አንድ ቡድን የሚለይበት ይሆናል።
ከውድድሩ ጅማሩ አንስቶ ሊጉን ያለ ተቀናቃኝ እየመራ የሚገኘው ሸገር ከተማ አስራ ሰባት ጨዋታ አድርጎ አርባ ሁለት ነጥብ በመያዝ ምድቡን እየመራ ይገኛል። ዛሬ 05:00 ላይ ከእንጅባራ ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የሚረታ ከሆነ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት በአርባ አምስት ነጥቦች ከወዲሁ ለ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉን የሚያረጋግጥ የመጀመርያው ቡድን ይሆናል።
በሌላ በኩል በሌላኛው የከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ሊጠናቀቅ የአምስት ጨዋታዎች ጊዜ ቢቀረውም በቡድኖቹ መካከል ቡርቱ ፉክክር እየተደረገበት መካሄዱን ሲቀጥል ምድቡን በሦስት ነጥብ ልዮነት የሚመራው ነገሌ አርሲ ጨምሮ ሀላባ ከተማ፣ ደሴ ከተማ እና ንብ በቀሪ ጨዋታዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት ሌላኛውን ወደ ሊጉ የሚያድገውን አንድ ቡድን የሚያሳውቀን ይሆናል።
የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን አራት ቡድን አውርዶ ሁለት ቡድን በማሳደግ በቀጣይ አመት ከአስራ ዘጠኝ ቡድን ቀንሶ በአስራ ስድስት ቡድኖች መካከል እንደሚካሄድ ይታወቃል።