ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ሸገር ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጓል

ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ሸገር ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጓል

18ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ሀ” ጨዋታዎች ዛሬ ሲገባደድ ሸገር ከተማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል።

የ2017 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በሁለት ምድቦች ተከፍሎ በሁለት ከተሞች እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን በሀዋሳ እየተከናወነ ያለው እና አስራ ስምንተኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የምድብ “ሀ” ጨዋታዎች ዛሬ በተከናወኑ ሁለት መርሃግብሮች ሲገባደድ ሸገር ከተማም በምስረታው የሁለተኛ ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገበትን ውጤት አስመዝግቧል።

ረፋድ ሦስት ሰዓት ሲል ሁለቱም በወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኙትን አምቦ ከተማ እና ዱራሜ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ አለምሰገድ አድማሱ ሁለት ምስጋና አገንሳ እና ትዕዛዙ መንግስቱ ለአምቦ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 4ለ1 ሲጠናቀቅ ከደመወዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ እየተፈነ ለሚገኘው ዱራሜ ከተማ መሪሁን መንቴ በፍፁም ቅጣት ምት የማስተዛዘኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል።

በመቀጠል አምስት ሰዓት ሲል ሊጉን በረጅም ርቀት እየመራ የነበረውን ሸገር ከተማን ከእንጅባራ ያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር አስመልክቶን በሸገር ከተማ የበላይነት ተጠናቋል። ሔኖክ አየለ ገና 5ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ጎል ሸገሮች መሪ መሆን ቢችሉም ሠለሞን ያለው ከሳጥን ውጪ ያስቆጠራት ግሩም ጎል እንጆባራን አቻ ያደረገች ቢሆንም ከአቻነት ጎሏ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን የሔኖክ አየለ ድንቅ ዕይታ ታክሎበት አቤኔዘር ኦቴ ሸገርን 2ለ1 በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ በይበልጥ በሁሉም ረገድ ብልጫውን ይዘው የተመለሱት ሸገሮች የመስዑድ ታምሩ አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት የታከሉበት ሁለት ጎሎች እና በምስጋና ሚኤሳ ተጨማሪ ጎል 5ለ1 አሸንፈዋል። በነገሌ አርሲ ቆይታው በተደጋጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ከጫፍ ሲደረስ የነበረው ወጣቱ አሰልጣኝ በሽር አብደላ ሸገር ከተማን በያዘበት የመጀመሪያ ዓመቱ ቡድኑን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀሪ አራት ጨዋታዎች እየቀሩ ወደ 2018 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ማሳደግ ችሏል።