ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ለቀጣይ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች በሀዋሳ ዝግጅታቸውን የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕና የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሠ እየተመሩ በፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎን በማድረግ ላይ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በቀሪ የሊጉ መርሃግብር ተጠናክሮ ለመቅረብ ቀደም ብለው ከማል ሀጂን ከሀላባ ከተማ ያስፈረሙ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ማምሻውን ስለማጠናቀቃቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

ክለቡን የተቀላቀለው ቀዳሚው ተጫዋች ማሞ አየለ ነው። በአጥቂ ስፍራ ላይ በቦዲቲ ከተማ ካለፈው ዓመት አንስቶ  እስከያዝነው አጋማሽ ድረስ በደብረብርሀን ከተማ በመጫወት በኋላም ከወር በፊት ደደቢትን በመቀላቀል እየተጫወተ የቆየው እና በከፍተኛ ሊጉ ግቦችን በማስቆጠር ጥሩ ጊዜ የነበረው አጥቂው በያዝነው ዓመት ሦስተኛው ክለቡ የሆነው የፕሪምየር ሊጉ ሀድያ ሆሳዕና በይፋ ተቀላቅሏል።

ሌላኛው የቡድኑ ፈራሚ የታንዛኒያ ዜግነት ያለው አማካይ አብዱላሂ ረዝኪ ነው ፤ ከዚህ ቀደም በኬኒያዎቹ ክለቦች ሞሮሆኒ ፣ ሶኒ እና ባንዳሪ እንዲሁም ደግሞ በቦትስዋናው ኦራፓ ከዓመት በፊት ደግሞ ለሀገሩ ክለብ ሲምባ የተጫወተው ይህ ተጫዋች የሙከራ ጊዜውን ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በስኬት ማጠናቀቁን ተከትሎ በይፋ ፊርማውን ለክለቡ አኑሯል።