ስሑል ሽረዎች የአምስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቅቀዋል

ስሑል ሽረዎች የአምስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቅቀዋል

ስሑል ሽረዎች ዕግዳቸው ተነስቶ አምስት ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ ከአንድ ተጫዋች ጋር በስምምነት ተለያይተዋል።

በሁለት ተጫዋቾች ውዝፍ ደሞዝ ምክንያት ዕግድ ላይ በመቆየታቸው ዝውውር ሳይፈፅሙ የቆዩት ስሑል ሽረዎች በስተመጨረሻ የተጫዋቾቹን ችግር መፍታታቸውን ተከትሎ ዕግዱ ተነስቶላቸው ተጫዋቾች አስፈርመዋል። የዝውውር መስኮቱ በትናንትናው ዕለት ቢዘጋም የተጫዋቾቹ ጉዳይ እስኪጠናቀቅ የአዳዲስ ተጫዋቾች ፊርማ በልዩ ሁኔታ በይደር የተያዘለት ክለቡ በዛሬው ዕለት አምስት ተጫዋቾች አስፈርሞ ከአንድ ተጫዋች ጋር በስምምነት ተለያይቷል።

ቡድኑን ለመቀላቀል በዛሬው ዕለት ፊርማቸው ያኖሩት ተጫዋቾች ደግሞ ከቡድኑ ጋር የነበረውን ውል አፍርሶ ወደ ሌላ ክለብ ለመቀላቀል በሂደት ላይ  የነበረው ተከላካዩ ነጻነት ገብረመድኅን ፣ ከአዳማ ሁለተኛ ቡድን ተገኝቶ ላለፉት ዓመታት በዋናው ቡድን ግልጋሎት በመስጠት ላይ የነበረው እና በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ቆይታ የነበረው በመስመር ተከላካይነት እና በአጥቂ ቦታ ላይ መጫወት የሚችለው ሁለገቡ አብዲ ዋበላ ፣ ላለፉት ስድስት ወራት በወልዋሎ ቆይታ የነበረው የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሸገር ከተማ የመስመር ተጫዋች አላዛር ሽመልስ ፣ ላለፈው አንድ ዓመት በሲዳማ ቡና ቆይታ የነበረው እና በ2016 በአንደኛ ሊጉ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ መለያ 13 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው አጥቂው ሔኖክ ፍቅሬ እንዲሁም የአምቦ ፕሮጀክት ውጤት የሆነው እና ላለፉት ዓመታት በሻሸመኔ ከተማ ቆይታ ያደረገው ተከላካዩ ኢቢሳ ከድር ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ቀደም ብለው ከፋሲል ገብረሚካኤል፣ አዲስ ግርማ እና ዮሴፍ ኃይሉ ጋር የተለያዩት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ ከግራ መስመር ተከላካዩ ሸዊት ዮሐንስ ጋር በስምምነት ተለያይተዋል።
ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተገኘው እና ከዚህ  ቀደም ለአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ለወጣት ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች ከዓመታት የስሑል ሽረ ቆይታው በኋላ በዛሬው ዕለት ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየት ችሏል።