ለሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጫወተው ተጫዋች በጨዋታ ማጭበርበር ክስ ተመሰረተበት።
የቀድሞ ኬንያዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ የጨዋታን ውጤት ለማጭበርበር ሲደራደር የሚያሳይ በሚስጥር የተቀዳ ተንቀሳቃሽ ምስል ተገኝቶበታል በሚል በሀገሩ ኬንያ ክስ ቀርቦበታል።
ተጫዋቹ በአንድ ተሽከርካሪ በቀኝ የኋላ መቀመጫ ላይ ተቀምጦ ከካሜራ ውጪ ከሆነ ሰው ጋር ሲደራደር በተንቀሳቃሽ ምስሉ የሚታይ ቢሆንም ምስሉ የተቀረፀበት ትክክለኛ ቀን አልታወቀም።
ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨምሮ ለቱስካር፣ ፖስታ ሬንጀርስ እና ልዮፓርድስ የተጫወተው ይህ ግብ ጠባቂ ከዚህ ቀደምም መሰል ተግባራት ላይ ሲሳተፍ እንደቆየም ብዙዎች እየጠቀሱ ይገኛሉ፤ በአሜሪካ ቴክሳስ የሚገኘው ‘ኬንያ ሪፖርትስ’ የተባለ መገናኛ ብዙሐን ተጫዋቹ በጨዋታ ማጭበርበሮች እየተሳተፈ እስከ 12 ሚልዮን የኬንያ ሽልንግ እንዳገኘም ይፋ አድርጓል።
በሁለት አጋጣሚዎች የኬንያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመሆን የተሸለመው ተጫዋቹ በጨዋታ ማጭበርበር ላይ ተሳትፏል የሚለው ዜና ይፋ ከሆነ በኋላ ጉዳዩ በኬንያዊያን ጨምሮ በሀገራችን እግር ኳስ ቤተሰብ ዘንድ ከፍተኛ መነጋገርያ ከመሆን በዘለለ ከዓመታት በፊት በተከናወኑ ጨዋታዎች ላይ የተከሰቱ አጠራጣሪ ክስተቶችን በተንቀሳቃሽ ምስል እያስደገፉ ቁጣ እና ቁጭታቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።
ከደቂቃዎች በፊት የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ያወጣ ሲሆን ፌደሬሽኑ በማህበራዊ ትስስር ገፆች በመዘዋወር ያሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተመለከተ መሆኑን በመግለፅ ከፊፋ፣ ካፍ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ምርመራ መጀመሩንም እንዲሁ ገልጿል።