የኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ ሸገር ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ግማሽ ፍፃሜው ተቀላቅለዋል።
ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሸጋገረው የኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በተደረጉ ሁለት መርሃግብሮች ተጀምሯል። ቀዳሚ የነበረው የባህርዳር ከተማ እና ሸገር ከተማ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክርን አስመልክቶን በከፍተኛ ሊጉ ሸገር ከተማ አሸናፊነት ተቋጭቷል። ጅሮም ፊሊፕ ገና በ7ኛው ደቂቃ ላይ በክፍት የጨዋታ ባስቆጠራት ጎል ባህርዳርን መሪ ያደረገ ቢሆንም ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሸገሮች ቅያሪያቸው ፍሬ ያፈራበትን እንቅስቃሴ ከማድረጋቸው ባለፈ ተቀይሮ የገባው ሙሉቀን ተስፋዬ 76ኛው ደቂቃ ላይ ከሰላሳ ሜትር ርቀት አካባቢ አላዛር ማርቆስ መረብ ላይ ያስቆጠራት ግሩም ጎል ጨዋታው በመደበኛ ደቂቃ 1ለ1 እንዲጠናቀቅ ሆኗል ፤ አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት ባመራው ጨዋታ ሸገር ከተማዎች በግብ ጠባቂያቸው አቤል ብቃት ታግዘው ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
በመቀጠል በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተከናወነው የሲዳማ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ በሲዳማ የበላይነት ተቋጭቷል። በመጀመሪያው አርባ አምስት ከእንቅስቃሴ ውጪ ብዙም በሙከራዎች መታጀብ ያልቻለው ጨዋታ ከዕረፍት መልስ ሲመለስ ግን ሲዳማ ቡና በተሻለ አቀራረብ የተመለሰበት ነበር። 71ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከቀኝ ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ታደሠ ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ ሲያደርግ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ብርሀኑ በቀለ እጅግ አስናቂ ኳስን ከሳጥን ውጪ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎ ጨዋታው ወደ 2ለ0 ተሸጋግሯል። በአጋማሹ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ይገዙ ቦጋለ ተጨማሪ ግብን በማከል ጨዋታው በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ሸገር ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ወደ ቀጣዩ ዙር ያሸጋገረው ውድድር ነገም ሲቀጥል መቻል ከኢትዮጵያ መድን ሀዋሳ ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር ይጫወታሉ።