የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የሚደረግበት ቦታ ታውቋል

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የሚደረግበት ቦታ ታውቋል

ስምንት ቡድኖች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የሚደረግበት ቦታ ታውቋል።

አርባ አራት ቡድኖችን በአራት ምድቦች ተከፍለው በአራት የተለያዩ ከተሞች ሲደረግ የነበረው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በሰበታ እና ሀዋሳ ከተሞች ላይ በተከናወኑ የምድብ “ለ” እና “ሐ” የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ፍፃሜውን አግኝቷል።

በቀጣዩ የ2018 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አራት ቡድኖችን በሚያሳውቀው በዚህ ውድድር ከምድብ “ሀ” ባቱ ከተማ እና ቡራዩ ክፍለ ከተማ ከምድብ “ለ” ቢሾፍቱ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከምድብ “ሐ” ሐረር ከተማ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ከምድብ “መ” መንጌ ቤኒሻንጉል እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወደ ማጠቃለያው ማለፋቸው ሲረጋገጥ አስራ ስድስት ቡድኖች ደግሞ ከአንደኛ ሊጉ የወረዱ ሲሆን በፕሪምየር ሊጉ የተሳተፉትን ጅማ አባጅፋር እና ጅማ አባቡና ከወረዱት ቡድኖች መካከልም ይጠቀሳሉ።

በሰበታ ከተማ የሚደረገው እና አራት ቡድኖችን ለከፍተኛ ሊጉ የሚያበቃው ውድድር ሚያዝያ 19 የሚጀመር ይሆናል።